በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቴክኖሎጂ ፋክልቲ መምህራን ለሕዳሴው ግድብ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ገለፁ
አዲስ አበባ፤ ሀምሌ 20/2004 (ዋኢማ) - የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስና ቴክኖሎጅ ፋክልቲ መምህራን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መሳካት በተሰማሩበት ሙያ አገራዊና ወገናዊ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ፡፡
የፋክልቲው መምህራንና ሠራተኞች የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በጎበኙበት ወቅት የዩኒቨርስቲው የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ንጉሴ ረታ እንዳሉት በግድቡ ግንባታ ላይ መምህራኑ አስተዋጽኦ ማድረግ ይፈልጋሉ፡፡
የዓባይ ጉዳይ ለመንግሥት ብቻ የሚተው ባለመሆኑ ለፕሮጀክቱ ስኬታማነት መምህራን ከገንዘብ ድጋፍ ባሻገር በሙያቸው ለማገልግል ከምንጊዜውም በላይ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ እንዳሉት በተፈጥሮ ሳይንስ ዘርፍ የተሰማሩ ምሁራን ለአገሪቱ ዕድገትና ብልጽግና የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ማናጀር ኢንጂነር ስመኘው በቀለ በበኩላቸው የግድቡ የግንባታ ስራ እየተፋጠነ ሲሆን፤ ግንባታው በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል፡፡
ግድቡ በአፍሪካ የመጀመሪያውና በዓለም ሰባተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት እንደሆነ የጠቀሱት ኢንጂነር ስመኘው በክረምቱ ዝናብ ስራው እንዳይስተጓጎል ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
በዓባይ ወንዝ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ከተሰሩ አራት ድልድዩች በተጨማሪ አምስተኛው ድልድይ በቅርቡ ግንባታው የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ለስራው ተደራሽነት ያላቸው መንገዶችም መገንባታቸውንም አስረድተዋል፡፡
ከጎብኚዎቹ መካከል ፕሮፌሰር ለገሠ ነጋሽና ዶክተር አስፋው ወሰን አስራት ግድቡ የአገር ኩራት መሆኑን ገልፀው፤ የግደቡን ግንባታ በአካል ተገኘተው በመጎብኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ከ50 በላይ የፋክልቲው መምህራንና ሰራተኞች ተካፋይ ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ከአራት ሺህ በላይ ሠራተኞች ግንባታውን ለማፋጠን ቀንና ሌሊት እየሰሩ እንደሚገኙ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


