የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በብሔራዊ ቤተ መንግስት አሸኛት ተደረገለት

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2004 (ዋኢማ) - በ30ኛው የለንደን ኦሎምፒክ ላይ ለሚሣተፈው የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን ቅዳሜ ሐምሌ 14 ቀን 2004 በብሔራዊ ቤተ መንግስት አሸኛኘት ተደረገለት፡፡

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ቡድኑ የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባትና የአገሪቱን የኦሎምፒክ ውጤት ለማስጠበቅ እንዲጥር አሳስበዋል፡፡

ቡድኑ የኢትዮጵያን ቀደምት አትሌቶች ፈለግ በመከተል የሀገርን ገጽታ ለመገንባትና ውጤታማ ለመሆን በሚደረገው ተሳትፎ የመንግስት ድጋፍ እንደማይለየው ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽነር አቶ አብዲሳ ያደታ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ተሳትፎ የተሳካ እንዲሆን መንግስትና ህብረተሰቡ ያደረጉት ድጋፍ ታላቅ ቦታ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኔ ኪዳነማርያም የኦሎምፒክ ቡድኑ ዝግጅት እንዲሳካ የተባበሩትን አካላት ሁሉ አመስግነዋል፡፡

አትሌቶቹን በመወከል የተናገረው አትሌት ገ/እግዚአብሔር አሁን ከእኛ የሚጠበቀው ውጤት ማምጣት ነው ሲል ገልጿል፡፡

በአሸኛኘት ስነስርዓቱ ላይ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በበርካታ የኦሎምፒክ መድረኮች ላይ ከፍ ብሎ የተውለበለበውን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለአትሌቶቹ ተወካዮች ቀነኒሳ በቀለና መሰረት ደፋር አሰረክበዋለ፡፡

አትሌቶቹም እስካሁን በተደረገው ዝግጅትና አጠቃላይ ሁኔታ ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በብሔራዊ ቤተ መንግስት በተደረገው የአሸኛኘት ስነ ስርዓት ላይ የሁለቱም ምክር ቤቶች አፈ ጉባኤዎችን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣኖች ተገኝተዋል፡፡

እንደ ኢሬቴድ ዘገባ የኢትዮጵያ የኦሎምፒክ ቡድን ከማክሰኞ ሐምሌ 17 ቀን 2004 ጀምሮ ወደ ስፍራው ይጓዛል፡፡

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 249 guests