ፕሬዝዳንት ግርማ የሞዛቢክ አምባሳደርን አሰናበቱ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 19/2004 (ዋኢማ) - ፕሬዝዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ላለፉት ስድስት ዓመታት በኢትዮጵያ ያገለገሉትን የሞዛቢክ አምባሳደር አሰናበቱ።
ፕሬዚዳንት ግርማ አምባሳደሩ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ለሁለቱ አገራት ግንኙነት መጠናከር ላደረጉት አስተዋጽኦ አመስግነዋል።
ሁለቱ አገሮች በተመሳሳይ ሁኔታ በፈጣን የልማት እድገት ላይ ያሉ አገራት መሆናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ መድረኮች በጋራ ተባብረው መስራታቸውን የበለጠ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ በቀጣይ የሚሾመው አዲሱ የአገሪቱ አምባሳደርም የቆየውን የሁለቱን አገራተ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር ረገድ ብዙ ጥረት ያደርጋል ብለው ተስፋ እንደሚያደረጉም ገልጸዋል። ተሰናባቹ የሞዛምቢክ አምባሳደር ማኑኤል ቶማስ ሉቢስ በበኩላቸው እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ በኢትዮጵያ በነበራቸው የስድስት ዓመታት ቆይታ በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ፈጣን የልማትና የማህበራዊ ለውጥ መደነቃቸውን ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ውጭ የሚገኙ አካባቢዎችንና ከተሞችን ተዘዋወረው የመጎብኘት እድል እንደነበራቸው የገለጹት አምባሳደሩ ለውጡ ኢትዮጵያ ወደፊት በአፍሪካ አሕጉርና በዓለም አቀፍ መድረኮች ከፍተኛ ተደማጭነት እንደሚኖራት የሚያመላክት ነው።
በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ከአየር ትራንስፖርት ባሻገር በሌሎች የንግድ መሰኮችም ለመደገፍ አገራቸው ጥረት እያደረገች ነው።
ሞዛምቢክ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጅትን ልምድና አሰራር ለመቅሰም፣ በግብርና በድርና ማግ እንዲሁም በኮብልስቶን መስኮች ተሞክሮ ለመውሰድ የሚያስችላትን የትብብር ግንኙነትም እያደረገች ነው። ኢትዮጵያና ሞዛምቢክ በይፋ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ ከ1983 ጀምሮ ነው።
እንደ ኢዜአ ዘገባ ኢትዮጵያ የሞዛምቢክን ጉዳይ ምትከታተለው ዚምባቡዌ በሚገኘው ኤምባሲዋ በኩል መሆኑን አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ ዲፕሎማት ገልጸዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


