ማህበሩ 16 ሚሊየን የሚሆኑ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ማድረጉን አስታወቀ
አዲስ አበባ ሐምሌ 18/2004/ዋኢማ/- የኦሮሚያ ልማት ማህበር ባለፉት 19 አመታት በክልሉ የሚገኙ ከ16 ሚሊየን በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማከናወኑን አስታወቀ።
የልማት ማህበሩ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በላከው መግለጫ፤ ማህበሩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ 130 የሚሆኑ መደበኛ ትምህርት ቤቶችንና 137 መሰረታዊ የአማራጭ የትምህርት ማዕከላትን በማቋቋም ለበርካታ ህፃናትና ወጣቶች የትምህርት እድል እንዲያገኙ አስችሏል።
በተጨማሪም ከ13 በላይ የጤና ማዕከላትን በመገንባት በክልሉ ያለውን የጤና አገልግሎት እንዲሻሻል በማድረግ በኩል የራሱን አስተዋፅኦ የተወጣ ሲሆን፤ 51 የጤና ኬላዎች፣ 38 የጤና ጣቢያ እና 36 ክሊኒኮችን በመገንባት በርካቶች የህክምና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማስቻሉን መግለጫው ጠቁሟል።
በክልሉ ሶስት የሚሆኑ መካከለኛ መጠን ያላቸው የመስኖ ልማት ስራዎችን በማከናወን በርካታ የክልሉ የገጠር ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የልማት ማህበሩ መግለጫ ይገልፃል።
እንደ መግለጫ በማህበሩ የንፁህ መጠጥ ውሃና የሳኒቴንሽን ፕሮግራሙ አማካኝነት በክልሉ 1ሺ 222 የውሃ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ነዋሪዎቹ ንፁህ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኙ አስችሏል።
ልማት ማህበሩ ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በክልሉ የሚያስፈልጉ የተለያዩ የልማት አውታሮችን በማሟላት በኩል ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጠል መግለጫው ገልጿል።
የልማት ማህበሩ በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እ.ኤ.አ በ1993 ለትርፍ ያልተቋቋመ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
| < Prev | Next > |
|---|


