ሂዮመን ራይትስ ዎችና የክህደት ክሶቹ!
አንማው ክንዴ
ሂዮማን ራይትስ ዋች ከወር በፊት አዲስ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይሄንኑ መግለጫም የተለያዩ ሚዲያዎች ሲቀባበሉት ሰንብተዋል፡፡ ሂዮማን ራይትስ ዎች፤ አምነስቲና ሲፒጂ (የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ ድርጅት )ሁሉም መሰረታቸውን አሜሪካ ያደረጉ ለዓለም ሰብአዊ መብት፤ የፕሬስ ነጻነት፤ የጋዜጠኞች መብት ፣ ለመንግስት ተቃዋሚዎች መብት፤ ወዘተ በመከራከር ስም የአሜሪካንን ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት ለማስከበር በሽፋን የሚሰሩ ድርጅቶች መሆናቸው ይታወቃል፡፡
የምዕራቡ ዓለም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተከተለው አዲስ የፖሊሲ አቅጣጫ የተለያዩ ስም ያላቸውን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማቋቋምና ከጀርባም በፋይናንስ በማገዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ በየሀገሩ ገብተው እንዲሰሩ አድርጓል፡፡ ሌላውና ተጠቃሹ ከመንግስት ነጻ የሆነ ፕሬስ በእነሱ አጠራር (Independent press) በራሳቸው አምሳል እንዲስፋፋና እንዲጠናከር ግፊት ማድረግ በተዘዋዋሪም በፋይናንስና ስልጠና መርዳትን ዋነኛ ስልት አድርገውት ኖረዋል፡፡ ምዕራባውያኑ መንግስታዊ ያልሆኑ አንዳንድ ድርጅቶችን በተለያየ ስም በማቋቋም በየሀገራት እንዲስፋፋ ሲያደርጉና ለግሱ ፕሬስ ሲሟገቱ ምን ዓይነት ተልእኮን እንደሚያሳኩላቸው አቅደው በማሰብ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን ትክክለኛና እውነተኛ ዓላማ ይዘው በመንቀሳቀስ ህብረተሰቡን የሚያገለግሉና በዚህም ፋይዳ ያለው ስኬት እያስመዘገቡ ያሉ በርካታ የዕርዳ ድርጅቶችና ማህበራት የሉም ማለት እንዳልሆነ አንባቢዎቼ ልብ እንዲሉልኝ እጠይቃለሁ፡፡ እነዚህኞቹ የሚንቀሳቀሱባቸውን ሀገራት ሕግ አክብረውና የህብረተሰቡን ትክክለኛ ተጠቃሚነት ብቻ ማዕከል አድርገውና የተቋቋሙበትን ዓላማ ለማሳካት እንደመስራታቸው በእርግጥም በመንግሥትና በህብረተሰቡ ሊበረታቱና ሊደገፉ ይገባል፡፡
ከነዚህ በተጻራሪ የሚገኙ ጥቂት የማይባሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ የውጭ የዕርዳታ ድርጅቶች (የልማት የእርዳታ) የትምህርት፣ የሰብአዊ መብት፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፤የጤና፤ድሆችን የሚረዳና የሚያቋቁም ተቋም ፣ የጉዲፈቻ ወዘተ … በሚል የተለያዩ ስሞችን በመያዝ በስፋት በሕዝቡ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱ ተልዕኮ ተሰጥቶአቸው ይሰማራሉ፡፡ ይህም በገቡባቸው ሃገራት ሁሉ ሕዝቡን በተሻለ ሁኔታ በቅርበት ለማግኘት በሚል ሽፋን ከቦታ ቦታ በቀላሉ እንዲንቀሳቀሱ ዕድል ይፈጥርላቸዋል፡፡ ከነዚህ መካከልም አንዳንዶቹ ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ በልማትና በእርዳታ ስራ ሽፋን በየስፍራው በመንቀሳቀስ የሚያገኙትን ወሬ ሁሉ እየለቀሙ በአሉታዊ መልኩና ለራሳቸው አላማ በሚጠቅም መልኩ በማቀናበር "መረጃ" በፍጥነት ወደ አሰማሯቸው አካላትና የፋይናንስ ድጋፍ ለሚያደርጉላቸው "ለጋሾች" ያስተላልፋሉ፡፡ ስለአንድ ሀገር ሕዝብና መንግስት፡ ስለአስተዳደሩ፡ስለመንግስታዊ መዋቅሩ፤ ስለፖለቲካ ፓርቲዎች፡ ስለግሉ ፕሬስ፤ ስለሰብአዊ መብት አያያዝ ወዘተ.. ስለ ሀገሪቱ የተፈጥሮ ሀብት፣ ወኪሎቻቸውን መድበው ያስጠናሉ፡፡ በዚህ ሽፋን የሀገራት ምስጢርና ጓዳ እየተበረበረና እየተፈተሸ ላቋቋሟቸው ድርጅቶችና የገንዘብ ድጋፍ ለሚያደርጉላቸው ተቋማት መረጃ ይላካል፡፡ ድሮ ድሮ የቅኝ ግዛት ማስፋፋት ጦርነት ከማካሄዳቸው በፊት ቄሶችና ሚሲዮናወያንን መጽሀፍ ቅዱስ አስይዘው በመላክ ነበር የሀገራትንና የመንግስታትን አቋምና ውስጠ ሚስጢር የሚያጠኑትና የሚያስጠኑት፡፡ ዛሬ ዘመኑም ቴክኒዮሎጂውም በመምጠቁ በትናንሽ የሞባይል ቀፎዎችና ላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ማንኛውንም መረጃ በደቂቃዎች ጊዜ ውስጥ ወደ የሀገራቸው ለማስተላለፍ ይችላሉ፡፡ ትልቁ ግባቸው የአጠኗትን ሀገር ሀብት እንዴት በወዳጅነት ቀርበውና ካምፓኒዎቻቸውን አስገብተው መዝረፍ እንደሚችሉና የሃገራቱን የፖለቲካ እንቅስቃሴ በበላይነት ለመቆጣጠር አለያም ቢያንስ ቢያንስ ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር ተጽእኖ ማሳደር የሚያስችላቸውን ሁኔታ ለመፍጠር ማሰባቸውና ማስላታቸው ነው፡፡ ለዚህም የሀገሪቱ መንግስት እነሱ እንዳሉት የሚሆንና የሚመቻቸው ከሆነ የፈለገው ጨቋኝና ረጋጭ ቢሆንም ደንታ አይሰጣቸውም፡፡ አብረውት ይቆማሉ፤ ይደግፉታልም፡፡ ለሀገሩ ብሔራዊ ጥቅምና መብት የሚከራከር ከሆነ ደግሞ ለእነሱ አልተመቸምና ተቃዋሚ ያደራጁበታል፤የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር አሉባልታና ሃሰተኛ ክስ በማቅረብ ዓለም አቀፍ ተጽእኖ እንዲያርፍበት የተቻላቸውን ሁሉ ከማድረግ አይቦዝኑም፡፡
ከዚህ ጎን ለጎንም በግሉ ፕሬስም አማካኝነት የማያቋርጥ ዘመቻ ይከፍቱበታል፡፡ ምክንያታዊ ባልሆነና ከራሳቸው ዓላማና ፍላጎት አንጻር ብቻ በተቃኘ ጉድኝት ከተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችና ሌሎች ኃይሎች ጋር በትብብርና በመደጋገፍ ይንቀሳቀሳሉ፤ጩኸታቸውንም አብረው ይጮኻሉ፡፡ ከዚህ በተጻራሪው ግን ብሔራዊ ጥቅሜን አሳልፌ አልሰጥም፤ ለውጭ ሃይሎች ፍላጎትም አልንበረከክም፣ እርዳታ ብትሰጡም በእኛ የውስጥ ጉዳይ እንድትገቡ አልፈቅድም፡ በማለት በጽናት በሚታገላቸው ጠንካራ መንግስትና ሕዝብ ላይ ሰፊ አሉባልታ፤ ሃሰተኛ ክስና ውንጀላ በመደርደር መልካም ገጽታውን ለማጠልሸት ሌት ከቀን ተግተው ይሰራሉ፡፡ በአንደኛ ደረጃ ከፍተኛ የስም ማጥፋትና የማጥላላት ዘመቻ የሚከፍቱት እነዚህ በሰብአዊ መብት በፕሬስ ነጻነት ጠበቃነት ስም የተቋቋሙት ዓለም አቀፍ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሲሆኑ አልፎ አልፎም በአንዳንድ የውጭ መንግስታት የገንዘብና የስለላ ተቋማት ከበስተጀርባ የሚደገፉ ናቸው፡፡
ክሳቸውና ወንጀላቸው ይቀጥላል…. ሰብአዊ መብት ይጣሳል፣ ዜጎች ይገረፋሉ፤ የፕሬስ ነጻነት የለም፤ ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፤ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ይታሰራሉ…ሌላም ሌላም ይላሉ፡፡
መንግሥታዊ ተቋማትንና ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎችንና ባለሥልጣናትን በሃሰተኛ ክስ ይወነጅላሉ፤ ሰፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ ይከፍታሉ፤ሌሎችንም በዚህ ዙሪያ በማሰለፍ ያስተባብራሉ፡፡
በኢትዮጵያ የበጎ አድራጎትና ማህበራት ሕግ ሲወጣ ጥቂት የውጭ ሃይሎች እንደልብ የፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ሥራ ለመስራት ይጠቀሙባቸው የነበሩ አንዳንድ ድርጅቶችን መግቢያ በር የሚዘጋባቸው መሆኑን ሲያውቁ ሕጉን በደፈናው ወደ ማጥላላትና መኮነን ነበር የገቡት፡፡ በቅድሚያ የሕጉን መሰረታዊ ዓላማ በግልጽ ተረድቶና አስፈላጊነቱን ወይም ጠቀሜታውን አምኖ በመቀበል ምናልባትም አንዳንድ ግልጽ ያልሆኑ ወይም ክፍተት አለባቸው ተብለው የሚታሰቡና ለአፈጻጸም የማያመቹ ጉዳዮች ካሉም በዚህ መልኩ ቢሻሻል ብሎ በቅንነት ገንቢ ሃሳብ መሰንዘርና ለውይይት ራስን ማዘጋጀት ወግ ያለው ነገር ይሆን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሳለ በአንድ ሉአላዊት አገር ይውስጥና የዜጎቿ ብቻ በሆነ ጉዳይ እንደፈለግነው ገብተን ፖለቲካውን ካልፈተፈትንና የራሳችንን ፍላጎትና ዓላማ በፈለግነው መልኩ በግልጽም ሆነ በስውር ማራመድ ካልቻልን በሚል ስሜት ብቻ በመነዳት ውዥንብር መንዛት፤ ከውስጥም ከውጭም ተቃውሞ መቀሰቀስና በመጨረሻም በተጽእኖ ሕጉን እናስቀለብሳለን ብሎ መነሳት ፍጹም የተሳሳተ አካሄድ ነው፡፡ ከውጭ የሚመጣው ማንኛውም እርዳታና ድጋፍ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ የራሱን "መልዕክት"፤ አላማና ፍላጎት አለያም ቢያንስ ቢያንስ የተወሰኑ ቅድመ ሁኔታዎችንና ግዴታዎችን ይዞ እንደሚመጣ እየታወቀ እነዚህ ወገኖች ግን ይህንን ሃቅ ሆን ብለው በመክዳት ተጨፈኑና እናሞኛችሁ፤ከዚህ ሲዘልም እጃችሁን እንጠምዝዝ ይሉናል፡፡
የእርዳታ ተቀባዩ አገር ሕግና፤አሰራርና ነባራዊ ሁኔታ የእነሱን ዓላማና ፍላጎት የማያሳካ መስሎ በታያቸው ጊዜም ለጋሽ አገራትና ድርጅቶች ለዚያች አገር አንዳችም እርዳታ እንዳይሰጡ ያግባባሉ ወይም ሎቢ ያደርጋሉ፡፡ ዘመቻቸውንም አመቺ የመሰላቸውን ወቅት እየጠበቁ አጠናክረው ይገፉበታል፡፡ አንዳንድ ተቃዋሚ ኃይሎችን ከጎናቸው በማሰለፍና እነሱን ብቻ የመረጃ ምንጭ በማድረግ ሃሰተኛ ሪፖርት ተብዬ እያጠናቀሩ መግለጫ ያወጣሉ፡፡ እድል ካገኙም ረድተውትና አግዘውት የእነሱን ፖሊሲ እንዲያስፈጽም በትረ መንግስት መቆናጠጥ እስኪችል ድረስ ከተቃዋሚው ጎን እስከመጨረሻው ውድቀትም ቢሆን አብረውት ይሰለፋሉ፡፡ በዛ ሀገር ሁከትና ብጥብጥ ትርምስ እንዲነግስ፣ ሁሉም ነገር ከመንግስት አቅም በላይ እንዲሆን ለማድረግና የመንግሥትን ሕጋዊ ቁጥጥርና ኃላፊነት ለመሸርሸር በወኪሎቻቸው አማካይነት ይሰራሉ፡፡ ከቻሉም እስከ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ድረስ የውስጥ ተቃዋሚውን በመጠቀም ጊዚያዊ መረማመጃቸው ከማድረግ አይቆጠቡም፡፡ ይህ ሁሉ ለእነሱ ፍላጎት ፍጹም የሚገዛና የሀገሪቱን ብሔራዊ ክብርና ነጻነት በመዳፈርና የዜጎችን አንጡራ ሀብትና ሲሳይ አሳልፎ የሚሰጥ እንዳሻቸው እንዲፈነጩባት የሚፈቅድላቸው አሻንጉሊት መንግስት እንዲኖር ወይንም እንዲፈጠር የሚያደርጉት ፖለቲካዊ ሴራ ነው፡፡
በታዳጊ ሀገራት ውስጥ ብሔራዊ ጥቅማቸውንና ክብራቸውን ጠንክረው በሚያስከብሩ የሀገር መሪዎችና መንግስታት ላይ ሌላው የሚከፈትባቸው ዘመቻ በሀገር ውስጥ ለውጭ ሃይሎች ፍላጎት በተገዙ አንዳንድ የግል ሚዲያዎችና በምዕራቡ ዓለም ይዞታ ስር በሚገኙ ሚዲያዎች አማካኝነት፣ ሕዝቡ ተበድሏል፣ ተርቧል፣ ዲሞክራሲ፣ የለም፤ ፕሬሱ ታፍኗል፤ የሰብአዊ መብት ረገጣ፣ እስርና ያለፍርድ ግድያ ተስፋፍቷል መሪዎቹ አምባገነኖች ናቸው፤ ወዘተ የሚለው ነው፡፡
ከዚህ አንጻር መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ አንዳንድ የግል ሚዲያዎችና ተቋማት በአፍሪካ፣ በአረቡ ዓለም፣ በኤሲያና በላቲን አሜሪካ ውስጥ ባሉ አንዳንድ ሀገራት ላይ የተጫወቱት አፍራሽ ሚና ቀደም ባሉት ዓመታት በስፋት ታይቷል፡፡ እንዳንድ የምዕራባውያኑ ድርጅቶች እቅዳቸው የተሳካላቸው ሲሆን ጥቂቶቹም ሁኔታው እንዳሰቡት ሳይሆንላቸው በኪሳራ የወጡበት ሁኔታም ነበር፡፡ ዜጎች ይኽ ለምን ሆነ? ከራሳችን በላይ የውጭ ሀይሎች ለምን ተቆርቋሪ ለመሆን ፈለጉ? የሚለውን ጥያቄ ከብሔራዊ ጥቅማቸው አንጻር በጥልቀት መመርመር ካልቻሉ አደጋው የከፋ ነው፡፡
ሂዩማን ራይትስ ዎች ቀደም ሲልም እንደ አምነስቲና ሲፒጂ ሁሉ በኢትዮጵያ የተገኘውን የኢኮኖሚ እመርታና በሀገሪቱ የተመዘገበውን ፈርጀ ብዙ የልማት እድገት ቢያውቁትም የእነሱ ፍላጎት ሌላ ነውና እውቅና ሊሰጡት አልፈለጉም፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ መንግስት ልዩ ፖሊስ በሶማሌ ክልል ጋሽሞ አውራጃ ራክዳ ተብላ በምትጠራ መንደር ከአካባቢው ሰዎች ጋር በተፈጠረው አለመግባባት 10 ሰዎችን ረሽኗል፤ ሌሎችም ታፍነው ተወስደዋል፤ በርካታ ሰዎች ደግሞ ተዘርፈዋል፡፡ የራክዳ ነዋሪ የሆነወ አብዲካኒ አብዱላሂ አብዲ ልዩ ፖሊስ ሕዝቡን ሲያንገላታ ለማስቆም ሲሞክር በፖሊሶች ተገደለ፡፡ ነዋሪውና የአብዲካኒ ቤተሰብ በወሰዱት የበቀል እርምጃ ሰባት ፖሊሶች ተገደሉ፡፡ እንደገና ልዩ ፖሊስ ወደ አካባቢው ተጠናክሮ በመመለስ የከፋ የበቀል እርምጃ ወስዶ 10 ሰው ወዲያው ገደለ፡፡ 24 ሰዎች ጠልፎና አፍኖ ወስዷል፤ ይህንንም አጣሪ ቡድኔ አጣርቷል፤ ሰለባ የሆኑትና በፍርሃት ወደ ሶማሌ ላንድ የሔዱትን ቤተሰቦች አነጋግሬአለሁ ወዘተ...... ይላል የሂዩማን ራይትስ ዎች መግለጫ፡፡ ሌስሌ ሌፍኮው የሂዩማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ም/ ዳይሬክተር ተፈፀመ የተባለውን ድርጊት በማውገዝ የኢትዮጵያ መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙትን ለፍርድ እንዲያቀርብ ወደፊትም ልዩ የፖሊስ ኃይል እንዲህ አይነቱን ድርጊት እንዳይፈጽም ሊቆጣጠርና ሊከታተል ይገባል ማለታቸውም በመግለጫው ተካቷል፡፡ ሃላፊዋ ይኸችው የአፍሪካ ቀንድ ሀገር ለጋዜጠኞች፣ ለእርዳታ ድርጅቶች፣ለሰብአዊ መብት ቡድኖችና ገለልተኛ ለሆኑ ተቆጣጣሪዎች በሯ ዝግ ነው፤አትቀበልም ሲሉም ኮንነዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በሶማሌ ክልል ሪፖርት ለማድረግ የሄዱ ጋዜጠኞችን አስሯል ፡ከሀገር አባሯል፡፡ ለጋሽ ሀገራት ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን በዛ አካባቢ እንድትቀበል ጥሪ ማድረግ አለባቸውም ብለዋል ፡፡
በ2008 የሂዩማን ራይትስ ዎች ምርመራና ማጣራት መሰረት የኢትዮጵያ መከላከያ ሃይልና፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር ከ2007 እስከ 2008 በነበረው ግጭት ሁለቱም የጦር ወንጀል ፈጽመዋል፡፡ በተለይ ግን የኢትዮጵያ ጦር ሀይል በፈፀመው ግድያ፣ ግርፊያና ድብደባ አስገድዶ መድፈርና ማፈናቀል በሰው ዘር ላይ በተፈጸመው ወንጀል መጠየቅ አለበት ይላል፡፡ ሂዩማን ራይትስ ዎችም ሆነ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ወይንም ሲፒጂ የምዕራቡን ዓለም ብሔራዊ ጥቅምና ፍላጎት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጠባቂና አስጠባቂ ጋሻ ጃግሬዎች ናቸው፡፡
ምነዋ ታዲያ በብዙ የዓለማችን ክፍሎች በአንዳንድ አሸባሪ ድርጅቶችና አማጽያን አለያም በአንዳንድ መንግሥታት አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት በተፈጸሙና እየተፈጸሙ ባሉ ጥቃቶች ንጹሃን ዜጎች ሲገደሉና ሲቆስሉ እነዚህን ኃይሎች ተጠያቂ ያላደረጉት? በአረቡ ዓለም ተቀስቅሶ የነበረውን ሕዝባዊ ንቅናቄ ተከትሎ የሊቢያ ከተሞች በተለይም ትሬፖሊና ሲርት በኔቶ ኃይሎች በጄት በተደበደቡባቸው ጊዚያት ሕጻናትንና ሌሎች አረጋውያንን ጨምሮ በርካታ ንጹሃን ዜጎች ሲረግፉ ሂዩማን ራይትስ ዎችና አምነስቲ ስንትና ስንት ሺህ ማይልስ አቋርጠው መጥተው የነበሩትን የውጭ ኃይሎችንም ሆነ የሊቢያ አማጽያንን በዘር ማጥፋት ሳይከሱአቸው ለምን ቀሩ?
ታዲያ የኢትዮጵያ ሰራዊት በራሱ ሀገርና ክልል ድንበሩንና ሕዝቡን ከአሸባሪዎች ለመጠበቅ በወሰደውና ራሱን ለመከላከል በሚወስደው እርምጃ እንዴት ነው በወንጀል ተጠያቂ የሚሆነው? የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተሰጠው ሕገ መንግስታዊ ሃላፊነትና ለባንዲራው በገባው ቃለ መሃላ መሰረት ሌሊትና ቀን በአራቱም ማእዘናት ዘብ ቆሞ የሀገሩን ዳር ድንበር ከወራሪዎች ከጠላት ሰርጎ ገቦች ከአሸባሪዎች የመጠበቅ ጥቃት ሲሰነዘርበትም አጸፋ የመመለስ ጠላቱን አሳዶ የመምታትና አካባቢውን ሰላም ከሚያደፈርሱ ሃይላት የማጽዳት ሃላፊነትም ግዴታም አለበት፡፡ አንድ ሰራዊት ጥቃት ሲሰነዘርበት እጁን አጣጥፎ ይመልከት የሚል ሕግ በዓለም ላይ የለም ሊኖርም አይችልም፡፡
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ትላንትም ሆነ ዛሬ ከምንም በላይ በዴሲፕሊን አክባሪነቱ ከፍተኛ ዝና ያለው፤ የጦርነት ልምድና ባሕል ያለው በዘመኑ ወታደራዊ እውቀትና ቴክኒዮሎጂ ታንፆ የተገነባ ፕሮፌሽናል ሰራዊት ነው፡፡ በዚህ ብቃቱና ዲሲፕሊኑ የተሰጠውን ግዳጅ በሚገባና በኃላፊነት መንፈስ የመወጣት ችሎታ ያጎለበተና የሕዝባዊነት ስሜት ያዳበረ ሕግ አክባሪ ሠራዊት ነው፤ በመንግስታቱ ድርጅት አለም አቀፍ ተልእኮዎች ላይ ሁሌም ተመራጭ የሚያደርገውም ይህ ዓይነተኛ ባህሪው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከቆዩት ኮርያና ኮንጎ፣ በተለይ ደግሞ ከቅርቦቹ ሩዋንዳ፣ ብሩንዲ፣ላይቤሪያና ዳርፉር ከበቂ በላይ ምስክሮች ናቸው፡፡ በበርካታ ታላላቅ የዓለም ሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ሥር የዘመተውና ግዳጁን በከፍተኛ ወታደራዊ ዲሲፕሊንና ብቃት ለተወጣውና አሁንም በተመሳሳይ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ለሚገኘው አኩሪ ሰራዊታችን ራሱን ተመድን ጨምሮ በተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ከፍተኛ የጦር አመራር አዛዦችና ኃላፊዎች ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው ነው፡፡ ይህ ምስክርነት እየተሰጠው ያለውን የኢትዮጵያ ሰራዊት በምን መስፈርት ነው ታዲያ ሂየማን ራይትስ ዎች በዝርፊያ፣ በሴት መድፈርና ሲቪሎችን በማንገላታት ወዘተ.. ተጠያቂ የሚያደርገው? የኢትዮጵያ ሰራዊት አሸባሪዎችን ሲያሳድድና ሲመታ ሕዝቡን ያከብራል፡፡ ልጆቹን አይደፍርም፤ ንብረታቸውን አይዘርፍም፤ ከቶውንም አያደርገውም፤ይልቁንም ዜጎችን ከተለያዩ የሽብር ጥቃቶችና ከደህንነት ስጋቶች ፍጹም ነጻ ለማድረግና ሰላማቸውንም በአስተማማኝ ለማስጠበቅ ነው በአስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ሆኖ በመስራት ላይ የሚገኘው፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዎች የመረጃ ምንጮች ራሳቸው አሸባሪዎቹ እንደሚሆኑ መጠራጠር አይቻልም፡፡ የእነሱን ቃል ሰምቶ ነው ተአማኒነት ያሳጣው ውንጀላ ውስጥ የገባው፡፡ የኢትዮጵያ ሰራዊት መሪዎች በእዝ ሰንሰለቱ መሰረት እስከመጨረሻው ወታደር ድረስ ቁጥጥር ያደርጋሉ፤፤ ሕገወጥ ድርጊት የፈጸሙና ከትእዛዝ ውጭ የሆኑ የሠራዊቱ አባላት ከተገኙም በማስረጃ ተደግፎ ተጠያቂ የሚሆኑበትና እርምጃ የሚወሰድበት የራሱ የሆነ ሕጋዊ አካሄዶች ያሉት ነው፡፡ ይህ ባለበት ሁኔታ የሂዩማን ራይትስ ውንጀላ በምንም መልክ ሚዛን የሚደፋ አይሆንም፡፡ ይልቁንም ራሱን ይበልጥ አጋልጦበ ትዝብት ላይ ጥሎታል፡፡
የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሰፊ በመሆኑ ከሌሎች አገራት ጋር ያዋስነናል፤ ከጅቡቲ፣ ከሶማሌ፣ ከሶማሌላንድ፡፡ ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጠው የጸጥታ ቀጠናና ወታደራዊ ዞን ነው፡፡ ከድንበሩ መስፋት ጋርም የአሸባሪዎች የመተላለፊያ መስመር ነው፡፡
በሶማሊያ የሚንቀሳቀሰው የአልቃይዳ ክንፍ የሆነው አልሸባብ ፣ አልኢትሀድ፣ የኦጋዴን ነጻ አውጪ ግንባር / አብነግ/ በዚሁ ክልል አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ራሱ ቢንላደን ሶማሊያ ውስጥ ለረዥም ጊዜ ቆይቶ ከ17 በላይ ማሰልጠኛዎች ለመክፈት ችሎ ነበር፡፡ ዛሬ ዓለም አቀፍ አሸባሪነት ነፍስ ዘርቶ ከሚንቀሳቀስባቸው አደገኛ አካባቢዎች መካከል የአፍሪካ ቀንድና አካባቢው አንዱ ነው፡፡ ሶማሊያ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ረጅም ድምበር የምትጋራ የጎረቤት አገር ናት፡፡ በሶማሊያ ውስጥ የነበረውን መንግሥተ አልባነትና ሥርአተ-አልበኝነት እንደምቹ ሁኔታ በመውሰድ አልቃይዳና ተቀጽላው አልሸባብ የሶማሊያንና የአካባቢውን ሰላም በማወክ ተግባር ላይ ትኩረት አድርገው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር ይታወቃል፡፡ እንዲህ በተወሳሰበ የጸጥታ ቀጠና ውስጥ አሸባሪዎች ሕዝቡ መሀል ተመሳስለው በመግባት ጥፋት የሚፈጥሩበት ሁኔታም አለ፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት ደግሞ የዜጎችንና የሃገር ደህንነትንና ሰላምን ለማረጋገጥ የጥፋት ኃይሎችን እንቅስቃሴ በመከታተል የማምከን ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ግዴታውንና ኃላፊነቱን በመወጣት ሂደት በጸረ ሰላም ኃይሎች ላይ ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ኪሳራ ሲያከናንባቸው እነሂዩማን ራይትስና መሰሎቻቸው የቁራ ጩኸታቸውን በመቀባበል ያሰማሉ፡፡
ኦጋዴን ውስጥ በኢትዮጵያውያንና በቻይና ዜጎች ላይ አሰቃቂ ግድያ የፈጸመውና ከዚህም በላይ የክልሉን ኗሪ ሰላማዊ ሕይዎት አደጋ ላይ ጥሎት የቆየውና ለብዙዎች አካባቢያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት የሆነው ማነው? ምእራባውያን ቱሪስቶችን እያሳደደ ከሚያፍነውና ከሚገድለው ጀርባ የተሰለፈው ፀረ ሰላም ኃይልስ ማነው? ይህ ሁሉ የአሸባሪዎችን የትብብር መረብ በግልጽ የሚያሳይ ፀረ ሰላም እንቅስቃሴ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊትም ሆነ ፖሊስ በሕጉ መሰረት የዜጎችንና የሃገሪቱን ሰላም የማስከበር ኃላፊነቱን በማናቸውም ጊዜና ስፍራ የመወጣት ህገመንግሥታዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ የሂዩማን ራይትስ ዎችን ወይንም የአምነስቲን ፈቃድ አይጠይቅም፡፡ ለአለም እጅግ አስጊ የሆነው ጽንፈኛና አክራሪ የሆነ አሸባሪነት እየተስፋፋ ያለው አንዱም ስፍራ የእኛው ቀጣና ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ለኢትዮጵያም፣ ለአፍሪካም፣ ለአለምም ታላቅ ጠንቅ ነውና ሂዩማን ራይትስ ዎች የበሬ ወለደ ቅጥፈቱን ቢያቆመው ይመረጣል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


