ሱዳናዊው የኦሳማ ቢን ላደን ሾፌር ወደአገሩ ተመለሰ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 12/2004 (ዋኢማ) - ኢብራሂም አልኮሲ የተባለው ሱዳናዊ የአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን የቀድሞ ሾፌርና ምግብ አዘጋጅ ወደ አገሩ መመለሱን የአገሪቱ ባለሥልጣኖችና አንድ የአካባቢ ራዲዮ ጣቢያ ሰሞኑን መግለጻቸውን ዘገባዎች አመለከቱ። ባለፈው ዓመት አቦታባድ በተባለችው የፓኪስታን ከተማ ውስጥ በአሜሪካ ባህር ኃይል ኮማንዶ ቡድን የተገደለው የአል ቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን የቀድሞ ሾፌርና ምግብ አዘጋጅ ኩባ ውስጥ ከሚገኘው የጓንታናሞ ወህኒ ቤት ወደ ሱዳን ሰሞኑን የተመለሰው በአሜሪካ ወታደራዊ አውሮፕላን መሆኑንም ዘገባዎች ጨምረው ገልጸዋል።

የኦሳማ ቢን ላደን የቀድሞ ሾፌርና ምግብ አዘጋጅ የነበረው ኢብራሂም አልኮሲ እ.አ.አ መስከረም 11 ቀን 2001 አሸባሪዎች በኒውዮርክ የንግድ ማዕከል ሁለት ሰማይጠቀስ ሕንፃዎችና በዋሺንግተኑ የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር ሕንፃ ጋር የጠለፏቸውን ግዙፍ የመንገደኞች ማመላለሻ አውሮፕላኖች በማ ጋጨት ከተፈፀመው አደጋ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ተጠርጥረው እንደተያዙት በርካታ አሸባሪዎች ሁሉ ከአስር ዓመታት በላይ በጓንታናሞ ወህኒ ቤት እንደቆየ ታውቋል። ግለሰቡ አፍጋኒስታን ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋለው አሜሪካ የአፍጋኒስታኑ የቀድሞ የታሊባን መንግሥት አደጋውን በማስፈፀም በግንባር ቀደምነት ተጠያቂ የሆነውን የአልቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደንን አሳልፎ ለመስጠት ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቶ በአሜሪካና በተባባሪዎቿ ጦርነት በተከፈተበት ወቅት እንደሆነ ተገልጿል። ግለሰቡ ጥፋተኛነቱን በማመኑ በእሥራት እንዲቆይ የተወሰነበት ጊዜ በሁለት ዓመት ተቀንሶለታል።

ዕድሜው በሃምሳ ዓመትና ከዚያም በላይ እንደሆነ የተገመተው ሱዳናዊ ኢብራሂም አልኮሲ የኦሳማ ቢን ላደን የቀድሞ ሾፌርና ምግብ አዘጋጅ በመሆን ብቻ ሳይሆን ኦሳማ ቢን ላደን በቁጥጥር ስር እንዳይውል ጠባቂ ሆኖ ሲከላከል በመቆየት ጭምር የሠራ ከመሆኑ አንፃር እ.አ.አ 2010 ውስጥ በ14 ዓመት እሥራት እንዲቀጣ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ተወስኖበት ነበር። ይህ ውሳኔ እ.አ.አ በ2011 በሁለት ዓመት ተቀንሶለታል። በዚህ መሠረት የእሥራት ጊዜውን ፈፅሞ ወደ አገሩ ሊመለስ ችሏል።

ኢብራሂም አልኮሲ ወደ አገሩ እንደተመለሰ የጓንታናሞ ወህኒ ቤት ቆይታው አስቸጋሪና ትክክለኛ ያልሆነ እንደነበር ማመልከቱን አሶሺየትድ ፕሬስ የኡምዱርማንን ራዲዮ በመጥቀስ ገልጿል።

ግለሰቡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የጓንታናሞ እስረኞችን በሚመለከት ባወጡት የተሻሻለ ፖሊሲ መሠረት በወታደራዊ ፍርድ ቤት ፊት ቀርቦ ውሳኔ ለማግኘት የመጀመሪያው እሥረኛ መሆኑንም አሶሽየትድ ፕሬስ ጨምሮ ገልጿል። በዚህ ፖሊሲ መሠረት ውሳኔ ያገኘው ኢብራሂም አልኮሲ እንደተጠቀሰው ሰሞኑን ካርቱም ገብቷል።

ኤኤፍፒ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቃባይን ጠቅሶ እንዳመለከተው ደግሞ ኢብራሂም አልኮሲ ካርቱም ከመግባቱ ቀደም ሲል የወታደራዊ አውሮፕላኑን በረራ በሚመለከት በአሜሪካና በሱዳን ባለሥልጣኖች መካከል አንድ ዓይነት ግንኙነት ሳይፈጠር አልቀረም። በአሜሪካና በሱዳን መካከል ያለው ግንኙነት ቀዝቃዛ እንደሆነ ይታወቃል።

የእስራት ጊዜውን ፈፅሞ አገሩ የገባው ኢብራሂም አልኮሲ አል ቃይዳን መደገፍ የጀመረው እ.አ.አ ከ1996 አንስቶ እንደሆነ ገልጿል። ከዚያም ተቀማጭነቱን የአፍጋኒስታን ደቡባዊ ምሥራቅ ከተማ በሆነችው ጃላላባድ ውስጥ ወደ አደረገው የአል ቃይዳ መሪ ኦሳማ ቢን ላደን ሠፈር በመሄድ መቀላቀሉን አረጋግጧል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 363 guests