በበጀት ዓመት ከ20 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ለመገንባት ታቅዷል-የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን
አዲስ አበባ፤ ሃምሌ 11/ 2004 (ዋኢማ) -በመላው አገሪቱ በተያዘው በጀት ዓመት ከ23 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከፍተኛ ጥገናን ጨምሮ ከ20 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታ ለማከናወን ማቀዱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዛይድ ወልደገብርኤል ትናንት የ2004 ዓ.ም የስራ አፈጻጸም ግምገማና የ2005 በጀት ዓመት ረቂቅ እቅድ ላይ ውይይት ሲካሄድ እንደተናገሩት በ2005 በጀት ዓመት በጠቅላላው 545 የመንገድ ፕሮጀክቶች ለማከናወን ታቅዷል፡፡
ከእነዚህ መካከል 52ቱ አዲስ የሚጀመሩ የመንገድ ስራዎች እንደሆኑና ሌሎች 35 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ደግሞ ቀደም ሲል የተጀመሩና በጀት ዓመት መጨረሻ የሚጠናቀቁ ናቸው ብለዋል፡፡
ቀሪዎቹ መደበኛና ወቅታዊ ጥገና፣ የጥናት ስራዎች የሚከናወንላቸውና ነባር ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በተጠናቀቀው የ2004 በጀት ዓመት የመደበኛና የጥገና ስራዎችን ጨምሮ 19 ሺህ 549 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ የተለያዩ የመንገድ ግንባታ ስራዎችን ለማከናወን አቅዶ የእቅዱ 98 በመቶ አከናውኗል ብለዋል፡፡
በእቅዱ መሰረት የተከናወኑት ስራዎች በመንገዶች ማጠናከር ማሻሻልና ግንባታ 89 በመቶ፣ በመደበኛና ወቅታዊ የመንገድ ጥገና 107 በመቶ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በአምስት ዓመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 14 ሺህ 728 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመስራት እቅድ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና በ2003/2004 ዓ.ም 38 ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ማጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ወቅት 39 አዳዲስ ፕሮጀክቶች መጀመራቸውን ጠቁመው በአጠቃላይ ከአምስት ዓመቱ እቅድ ውስጥ 35 በመቶ ያህሉ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በዚህም የአገሪቱ የመንገድ ሽፋን ከነበረበት 55 ሺህ 997 ኪሎ ሜትር ወደ 55 ሺህ 762 ከፍ ማለቱን አቶ ዛይድ አመልክተዋል፡፡
ባለሥልጣኑ በኮንትራት አስተዳደርና አመራር የነበረበትን ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻሻለ በመምጣቱ ቀሪውን 65 በመቶ እቅድ በሚቀጥሉት ሶስት ዓመታት ማከናወን እንደሚቻልም ባቀረቡት ሪፖርት ላይ መጠቆማቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


