ኢትዮጵያ የባርሴሎናውን ሻምፒዮና በሦስተኛነት አጠናቀቀች

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 10/2004 (ዋኢማ) - ከሐምሌ 10 እስከ 15 በስፔን ባርሴሎና ሲካሄድ በቆየው የወጣቶች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ከዓለም ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
በአርባ አራት የውድድር ዓይነቶች አንድ ሺ ስምንት መቶ ሃምሳ ስድስት አትሌቶች በተሳተፉበት አሥራ አራተኛው የወጣቶች የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ በተለያዩ ርቀቶች ሦስት የወርቅ፣ ሦስት የብርና አንድ የነሐስ በድምሩ ሰባት ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም ሦስተኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

ኢትዮጵያ ሜዳሊያዎቹን መሰብሰብ የቻለችው በመካከለኛ ርቀቶች ያሳተፈቻቸው ወጣት አትሌቶች ባስመዘገቡት ጣፋጭ ድል ነው። ለኢትዮጵያ ከተመዘገቡት ሦስት የወርቅ ሜዳሊያዎች በአሥር ሺ ሜትር ወንዶችና በአምስት ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታ የተገኘው ድል ነው።

በአሥር ሺ ሜትር ወንዶች ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ያስመዘገበው የአሥራ ስምንት ዓመቱ ይገረም ደመላሽ ነው። ይገረም በውድድሩ ከኬንያ አትሌቶች ጋር ተፎካክሮ የመጨረሻዎቹን ዙሮች ለብቻው በመሮጥ ማሸነፍ ችሏል። ይገረም በውድድሩ ያሳየው ብቃት ኢትዮጵያ በርቀቱ ወደፊት ተተኪ እንዳዘጋጀች ያመላከተ ነበር።

ቀሪዎቹ ሁለት ወርቆች የተመዘገቡባቸው የሴቶችና የወንዶች የአምስት ሺ ሜትር ድሎችም ኢትዮጵያ የምትታወቅበትን የመካከለኛ ርቀቶች ወደፊትም ተቆጣጥራ እንደምትቀጥል ፍንጭ የሰጠ ነው። በተለይም በሴቶች ቡዜ ዲሪባና ሩቲ አጋ ያደረጉት ፉክክር ኢትዮጵያ በወጣቶች የመካከለኛ ርቀት ምን ያህል እየሰራች እንደሆነ ያመለከተ ነው።

በወንዶች አምስት ሺ ሜትር ወርቅ ያስመዘገበው ሙክታር ኢድሪስም በሻምፒዮ ናው የተለየ ክስተት ነበር። ሙክታር በፓሪስ በዳይመንድ ሊግ ከሳምንት በፊት ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብ አሸንፎ በባርሴሎናው ሻምፒዮና ላይም ያንን ብቃቱን መድገሙ በርቀቱ ወደፊት ሊነግሥበት እንደሚችል አመላክቷል።

ኢትዮጵያ በዘንድሮው የወጣቶች ሻምፒዮና ያጠናቀቀችበት ደረጃ ካለፈው ሻምፒዮና ጋር ሲነፃፀር ለውጥ አሳይቷል። ባለፈው ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ሁለት የወርቅና ሦስት የብር ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ ከዓለም አምስተኛ ደረጃን ይዛ ስታጠናቅቅ ኬንያ ሰባት የወርቅ፣ አራት የብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያ ሰብስባ ከዓለም አንደኛ ሆና አጠናቃለች።

በባለፈው ሻምፒዮና ኬንያ በርካቶቹን ሜዳሊያዎች የሰበሰበችው ኢትዮጵያ በምትታ ወቅባቸው በመካከለኛ ርቀቶች በማሸነፍ ነው። በዚያ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ ድል ታደርጋለች ተብሎ በተገመቱት መካከለኛ ርቀቶች የተሳኩ ባይሆንም በዘንድሮ ሻምፒዮና ድል ተመዝግቦባቸዋል፡፡ በዘንድሮው ሻምፒ ዮና ኬንያ በርካታ ወርቅ የሰበሰበችበት አጭር ርቀት ለኢትዮጵያ መልካም አልነበ ረም። ካለፈው ሻምፒዮና ጋር ሲነፃፀርም ኢትዮጵያ በአጭር ርቀት ወጣቶች ላይ ብዙ መሥራት እንዳለባት የጠቆመ ነው።

በዘንድሮው ሻምፒዮና አሜሪካ በተለያዩ ርቀቶች ዘጠኝ የወርቅ፣ አራት የብርና ሰባት የነሐስ በድምሩ ሃያ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ አንደኛ ሆናለች።

ውድድሩ ሊጠናቀቅ አንድ ቀን እስኪቀረው የሜዳሊያ ሠንጠረዡን በሁለተኛ ነት ስትመራ የነበረችው ኢትዮጵያ ብትሆንም ኬንያ በውድድሩ መዝጊያ በተደረጉ የአጭር ርቀት ውድድሮች ተጨማሪ ሁለት ወርቅ በማግኘት የሁለተኛነት ደረጃን ከኢትዮጵያ ተረክባለች።

ኬንያ በወንዶች በስምንት መቶ ሜትር የብርና የነሐስ ሜዳልያ፣ በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የብር፣በአምስት ሺ ሜትር የነሐስ፣ በአስር ሺ ሜትር የብርና የነሐስ፣ በሦስት ሺ ሜትር የወርቅና የብር፣ በሴቶች አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር የብር፣ በአምስት ሺ ሜትር የነሐስ፣ በሦስት ሺ ሜትር የወርቅና የነሐስ በድምሩ አራት የወርቅ፣ አራት የብርና አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ማስመዝገብ ችላለች።
ይህም ኬንያ በወጣቶች የአጭር ርቀት ላይ ውጤታማ ለመሆን ጠንካራ ሥራ እየሰራች መሆኑን ያሳየ ነው። በአንፃሩ ኢትዮጵያ በአጭር ርቀት በሴቶች ሦስት ሺ ሜትር መሰናክል በጠጅነሽ ገቢሳ አማካይነት የብር ሜዳሊያ፣ በተመሳሳይ በሦስት ሺ ሜትር በሕይወት ገብረመድህን አማካኝነት የብርና በአንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር በሰንበሬ ተፈሪ አማካኝነት የነሐስ ሜዳሊያዎች ብቻ ናቸው የተገኙት።

ያለፈው ሻምፒዮና ላይ ሦስተኛ በመሆን ያጠናቀቀችው ኩባ ሦስት የወርቅና አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎችን በድምሩ አራት ሜዳሊያዎችን አግኝታ አራተኛ ሆና አጠናቃለች። ሁለት የወርቅና አራት የብር በድምሩ ስድስት ሜዳሊያዎችን ያስመዘገበችው ጀርመን አምስተኛ ሆናለች። ሩሲያ በበኩሏ ሁለት የወርቅ፣ ሦስት የብርና ሦስት የነሐስ ሜዳሊያዎችን አግኝታ ስድስተኛ ነች።

በአጭር ርቀቶች የአለምን ክብረወሰን በእጃቸው ያስገቡ አትሌቶችን ያፈራችው ጃማይካ ሁለት የወርቅ፣ ሁለት የብርና አንድ የነሐስ በድምሩ አምስት ሜዳሊያዎችን አግኝታ ሰባተኛ ደረጃን ይዛለች። አስር ቀናት የቀሩትን ሠላሳኛውን ኦሊምፒያድ የምታዘጋጀው እንግሊዝ ሁለት የወርቅ፣ አንድ የብር ሁለት የነሐስ በድምሩ በአምስት ሜዳሊያዎች ስምንተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች ሲል አዘ ዘግቧል።










  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 149 guests