ጉባኤው በሚካሄድበት ዕለት በሃይማኖት ሽፋን ህገወጥ ስብሰባ ለማካሄድ ጥሪ የሚያደርጉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ
አዲስ አበባ ሃምሌ 7/2004/ዋኢማ/ - የአፍሪካ ህብረት የመሪዎቹ ጉባኤ በሚካሄድበት ዕለት በሃይማኖት ሽፋን የተከለከለና ህገ-ወጥ ስብሰባ ለማካሄድ ጥሪ በማድረግ ላይ ያሉ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አሳሰበ።
ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ ጉባኤው በሰላም ተጀምሮ ይጠናቀቅ ዘንድ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የጸጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ዝግጅቱን አጠናቆ በስራ ላይ እንደሚገኝ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል ወርቅነህ ገበየሁ መናገራቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
በአንጻሩ ይህ ታላቅ የመሪዎች ጉባኤ በሚካሄድበት ዕለት ማለትም ሐምሌ 8 ቀን 2004 ዓ.ም ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተከለከለና ህገ-ወጥ ስብሰባ ለማካሄድ ጥሪ የሚያደርጉ ወገኖች እንዳሉ ታውቋል።
እንደ ፖሊስ መግለጫው የተከለከለና ሕገ-ወጥ ስብሰባውን ለማካሄድ የተወሰኑ ሀይሎች ከክልሎች ጭምር ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ እያደረጉ ያለበት ሁኔታ መኖሩን መግለጫው ጠቁሟል።
ሃይሎቹ በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ ወደጎን በመተው በአንዳንድ መስጊዶች በመግባት የጸሎት ፕሮግራሞችን ለህገ-ወጥ ቅስቀሳ በመጠቀም ላይ መሆናቸውንም መግለጫው ገልጿል።
በህገ-ወጥ ተግባሩ ለመተባበር ፈቃደኛ ያልሆኑ አማኞች፣ የሃይማኖት አባቶችና ኢማሞችን በመደብደብና በማስፈራራት የጸጥታ ሃይሎችንም በመተናኮል ኢ ህገ-መንግስታዊ ተግባር በመፈጸም ላይ መሆናቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
ይህን ስብሰባ በማስተባበር ላይ የሚገኙ ግለሰቦችም ህገ-ወጥ ጥሪ እያደረጉ መሆናቸውን ተገንዝበው ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ የፌደራል ፖሊስ በጥብቅ ያሳስባል።
ጥሪው ህገ-ወጥና ሆን ተብሎ በሀገሪቱ የተሰጣትን ከባድ አህጉራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ ታስቦበት የተጠራ መሆኑን በመገንዘብ፣ ሰላም ወዳዱ ህብረተሰብ በሂደቱ ባለመሳተፍ፣ ጥሪውን የሚያደርጉትን አካላትም በማጋለጥና ተዛማጅ እንቅስቃሴዎችን በመጠቆም የተለመደውን ትብብሩን እንዲያደርግ ጠይቋል።
ሐምሌ 2 የጀመረው 19ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በተለያዩ ስብሰባዎች ቆይታውን እስከ ሐምሌ 9 ቀን ድረስ ያደርጋል።
የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በሰላም ተጀምሮ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በትብብር በመስራት ላይ ይገኛል።
ህብረተሰቡም ለጉባኤው ስኬት የተለመደ ትብብሩን እያደረገ መሆኑን ነው ኮሚሽኑ ለኢሬቴድ የላከውን መግለጫ ጠቅሶ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
| < Prev | Next > |
|---|


