ከፌዴራል ፖሊስ የተሰጠ መግለጫ
ሀገራችን የምታስተናግደው አህጉራዊ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ከሐምሌ 2 እስከ 9 ቀን 2004 ድረስ ቋሚ መልዕክተኞችና አምባሳደሮች፣ ሚኒስትሮች ፣ የአህጉራዊና አለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎች፣ የአባል ሀገራት መሪዎች በሚገኙበት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በዚህ ስብሰባ ላይ የሚሳተፉ እንግዶችም ወደ መዲናችን ገብተዋል በመግባት ላይም ይገኛሉ፡፡ ስብሰባው በሰላም ተጀምሮ ይጠናቀቅ ዘንድ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ከሌሎች የፀጥታ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት ዝግጅቱን አጠናቆ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
ይህ በመዲናችን የሚካሄደው አህጉራዊ ስብሰባ በሰላም ተጀምሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ ወትሮም የሀገራችንን አንግዳ አክባሪነት ያስመሰከረው የኢትዮጵያ ህዝብ እና የመዲናችን አዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደተለመደው አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ መዲናችንና ነዋሪዎቿ ይህን ታላቅ ስብሰባ በስኬት እንዲጠናቀቅ ደፋ ቀና በማለት ላይ በሚገኙበት ወቅት አንዳንድ ግለሰቦች የመሪዎቹ ስብሰባ በሚካሄድበት እለት ማለትም ሐምሌ 8 ቀን 2004 ሐይማኖትን ሽፋን በማድረግ የተከለከለና ህገወጥ ስብሰባ ለማካሄድ ከክልሎች ጭምር ሰዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ጥሪ በማድረግ ላይ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በተጨማሪም እነዚህ ሃይሎች በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን ማሳሰቢያ ወደጎን በማለት በአንዳንድ መስጂዶች በመግባት የፀሎት ፕሮግራሞችን ለህገ-ወጥ ቅስቀሳ በመጠቀም ላይ ሲሆኑ፤ ለዚሁ ህገ-ወጥ ተግባር ለመተባበር ፈቃደኛ ያልሆኑ ምዕመናን፣ የሀይማኖች አባቶችንና ኢማሞችን በመደብድብ እና በማስፈራራት እንዲሁም የፀጥታ ሃይሎችን በመተናኮል ኢ ህገ- መንግስታዊ ተግባር በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡
ኮሚሽኑ ይህ ጥሪ ህገ-ወጥና ሆን ተብሎ ሀገራችን የተሰጣትን ከባድ አህጉራዊ ኃላፊነት ለመወጣት የምታደርገውን ጥረት ለማደናቀፍ ታስቦበት የተጠራ መሆኑን በመገንዘብ፣ ሰላም ወዳዱ ህብረተሰብ በሂደቱ ባለመሳተፍ ጥሪውን የሚያደርጉትን አካላት በማጋለጥና ተዛማጅ እንቅስቃሴዎችን በመጠቆም የተለመደውን ትብብር እንዲያርግ እየጠየቀ፣ ይህንን ስብሰባ በማስተባበር ላይ የሚገኙ ግለሰቦችም ይህ ጥሪ ህገ-ወጥ መሆኑ ታውቆ ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በድጋሚ በጥብቅ ያሳስባል፡፡ ( ኢሬቴድ)
| < Prev | Next > |
|---|


