ሳይንቲስቶች የአልዛይመር በሽታ ምልክት ከመታየቱ በፊት ማወቅ የሚቻልበት መንገድ እንዳለ አስታወቁ
በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ክፍል ያዋቀረው የሳይንቲስቶች ቡድን ከዘረ መል ጋር በተያያዘ የአልዛይመር በሽታ ስጋት የተጋረጠባቸው ቤተሰቦች ላይ ባካሄደው ጥናት ውጤት መሠረት በሽታው ከመከሰቱ ከ25 አመታት ቀደም ብሎ ምልክቶች ሊታዩ እንደሚችሉ በኒው ኢንግላንድ ጆርናል አስፍሯል፡፡ ሳይንቲስቶቹ የአልዛይመር በሽታ ምልክቶች ከመታየታቸው ቀደም ብሎ ሊጠቁም የሚችል መንገድ እንዳለ ይጠቁሟሉ።
የእንግሊዝ ኤክስፐርቶች እንደሚናገሩት የአልዛይመር በሽታ ከመከሰቱ አስቀድሞ የሚታዩትን ምልክቶችን መለየት የሚያስችል እውቀት መኖሩ በሽታውን በተሳካ ሁኔታ ለማከም የተሻለ እድል ይፈጥራል፡፡
ከእንግሊዝ፣ አሜሪካና ከአውስትራሊያ የተወጣጡ 128 ሰዎችን ያካተተው ጥናት የአልዛይመር በሽታ መንስኤ ሊሆኑ የሚችሉ ምልክቶችን በዘር የመተላለፉ እድሉ 50 በመቶ በሆነባቸው ሰዎች እንደተለመደው በ60ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ በሽታው ከመከሰቱ ይልቅ በ30ዎቹና 40ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡
ተመራማሪዎቹ በጥናቱ ውስጥ የተካተቱትን ሰዎችና የወላጆቻቸውን የጀርባ ታሪክ በማጥናት የተካሄደ ሲሆን፤ በሽታው መቼ እንደጀመራቸውና ምልክቶቹ ከታዩ ምን ያህል አመት እንዳስቆጠረ ከመተንተን በተጨማሪ የደምና የህብለ ሰረሰር ፈሳሽ ላይ ምርመራ በማካሄድ እንዲሁም የአዕምሮ ነርቭና ምዘና በማድረግ በጥናቱ የተካተቱ ሥራዎች ናቸው፡፡
በጥናቱ ውጤት መሠረት የበሽታው የመጀመሪያ ምልክት በህብለ ሰረሰር ውስጥ የሚገኝ ፈሳሽ መቀነስ ሲሆን፤ ይህም በሽታው ከመከሰቱ ከ25 አመት በፊት የሚታይ ይሆናል፡፡
ሌላው የበሽታው ምልክት ነው ተብሎ የተወሰደው፤ በ15 አመት ውስጥ የአንዳንድ የፕሮቲን አይነት በአዕምሮ ህዋሳት ላይ መጨመርና በአዕምሮ አካል ላይ የመጨማደድ ምልክቶች በሚታዩበት ጊዜ እንደሆነ ተቀምጧል፡፡ እንዲሁም በሽታው ከመከሰቱ ከአስር አመት በፊት እንደ ምልክት ይታያል ተብሎ የተቀመጠው የአዕምሮ ስኳርነት ያለውን ጉልኮስ አጠቃቀም በሚቀየርበት ጊዜና የተወሰነ የማስታወስ ችግሮች በሚስተዋሉበት ወቅት እንደሆነ ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡
የአልዛይመር ሶሳይቲ የምርምር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ክሊቭ ቦላርድ እንደሚናገሩት ይህ ወሳኝ ጥናት የሚያስገነዝበን በአዕምሮ ውስጥ የሚታዩ ቁልፍ ለውጦች በዘር ሃረግ ከሚተላለፉት የአልዛይመር በሽታዎች ጋር ተያያዥነት እንዳላቸውና እነዚህም ምልክቶች በሽታው ከመከሰቱ አስርት አመታት ቀደም ብለው መታየታቸው ለወደፊቱ በሽታውን ለመፈወስ ለሚደረገው ጥረት ፈር ቀዳጅ ይሆናል ብለዋል፡፡
ይህ ግኝት በሽታው ከመከሰቱ በፊት የሚታዩ ቁልፍ ምልክቶች በዘር በማይተላለፉትም የአልዛይመር በሽታዎች ጭምር ሊታዩ እንደሚችሉ ያመላከተ በመሆኑ እንደ ጥሩ ግኝት ተወስዷል፡፡
በእንግሊዝ የአልዛይመር የምርምር ማዕከል የምርምር ዳይሬክተር ዶክተር ኤሪክ ካራን በበኩላቸው፤ በዘር በሚተላለፉትም ሆነ በዘር በማይተላለፉት የአልዛይመር የበሽታ አይነቶች ላይ በቅድሚያ የሚታዩት ምልክቶች ተመሳሳይ ናቸው። በተጨማሪም የአልዛይመር በሽታ ህክምናን ቀደም ብሎ መሥጠት ውጤቱን ይበልጥ ስኬታማ እንደሚያደርገው ይታመናል ብለዋል፡፡
ሌላው የዚህ ጥናት ጥቅም የአልዛይመር በሽታን ገና በሂደት ላይ እንዳለ ማወቁ ታማሚ ሰዎች በአስቸኳይ ህክምናውን እንዲወስዱ ከማስቻሉም በላይ ለትክክለኛው ታማሚ በትክክለኛው ጊዜ አዲስ መድሐኒቶችን እንዲወስድ ይረዳል ብለዋል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


