የቆላ ዝንብን በጋራ ለማጥፋት የመግባቢያ ስነድ ተፈረመ

  • PDF

አዲስ አበባ ሀምሌ 6/2004/ዋኢማ/ - ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች ውስጥ የተንሰራፋውን የቆላ ዝንብ /ጸጼ/ በጋራ ለማጥፋት የአፍሪካ ኅብረትና የዓለም የእርሻ ድርጅት /ፋኦ/ አዲስ አበባ ውስጥ የመግባቢያ ስነድ ተፈራረሙ፡፡

የቀንድ ከብትና የዱር እንስሳትን በመግደል የሚታወቀውን የገንዲ በሽታ አምጭ ዝንብ በጋራ ለማጥፋት የሚያስችላቸውን ስምምነት የፈጸሙት በአፍሪካ ኮሚሽን የገጠር ኢኮኖሚና ግብርና ኮሚሽነር ሚስስ ሮዳ ቱምሲሚና በኅብረቱ የዓለም የእርሻ ድርጅት ተጠሪ ዶክተር ካስትሮ ካማራዳ ናቸው፡፡

ኮሚሽነሯ ከፊርማ ስነ-ስርዓቱ በኋላ ከሰሃራ በታች ያሉ የአፍሪካ አገራት በገንዲ አምጪ የቆላ ዝንብ ሳቢያ የገንዲ በሽታ የቀንድ ከብቶቻቸውን በብዛት እንደሚገድልባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህም በርካታ አፍሪካውያን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ አዳጋች እንደሆነባቸው ጠቁመው፤ የገንዲ በሽታ በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰትና በሽታውን አምጪ የሆነውን የቆላ ዝንብ ለመከላከል የሚያስችል መርሃ- ግብር በየዓመቱ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ገንዲ አምጪውን የቆላ ዝንብ ለማጥፋት ሁለቱ ተቋማት በጋራ የትብብር ስራ ለማከናወን የሚያስችላቸውን የመግበቢያ ሰንድ መፈረማቸው ከሰሃራ በታች የሚኖሩ አፍሪካውያን የምግብ ዋስትና የሆኗቸውን የቀንድ ከብት ከእልቂት መታደግ እንደሚቻል አመልክተዋል፡፡

የዓለም የእርሻ ድርጅት በጋራ ለመስራት ከሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሱ ለገንዲ በሽታ መወገድ እንዲሁም ለአርሶ አደሩና ለአርብቶ አደሩ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያለውን ጽኑ አቋም ያመለክታል ብለዋል፡፡

በኅብረቱ የዓለም እርሻ ድርጅት ተጠሪ ዶክተር ካስትሮ ካማራዳ በበኩላቸው የተደረሰው ስምምነት ትክክለኛ እርምጃ መሆኑን ጠቁመው፤ ወደፊት ከመላው አፍሪካ የቆላ ዝንብና የገንዲ በሽታ ማጥፊያ ተቋም ጋር ድርጅቱ በጋራ ለመስራት መነሻ ይሆነዋል ብለዋል፡፡
በቆላ ዝንብ አማካኝነት በቀንድ ከብት ኃብት ላይ የሚስፋፋውን የገንዲ በሽታን ለማጥፋትና በወረርሽኝ መልክ እንዳይከሰት ለመግታት ኢትዮጵያና ጋና በአህጉራዊ ደረጃ በሽታውን በዘመቻ ለማስወገድ በተቋቋመው ድርጅት /ፓቴክ/ አማካይነት የብድር ድጋፍ እያገኙ ነው፡፡

ቦትስዋና፣ ናሚቢያ፣ አንጎላ፣ ዛምቢያና ዚምባብዌ በራሳቸው የገንዘብ አቅም የገንዲ በሽታን ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል በምትገኘው ዚምባብዌ ውስጥ የሚገኘው የዛምቤዚ ሸለቆ በቆላ ዝንብ ወረርሽን ክፉኛ የተጠቃ ነው፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ የዚምባብዌ ባለስልጣናት የመከላከያ መድሃኒቱን በአውሮፕላን ርጭትና በሌሎች ዜዴዎች ለመጠቀም ሲገደዱ ኢትዮጵያ ደግም በቅርቡ በደቡብ ስምጥ ሸለቆ ያለውን የዝንብ ቁጥር ለመቀነስ የመከኑ ዝንቦችን በአውሮፕላን በመታገዝ ከአየር ወደ ምድር የመልቀቅ ተጓዳኝ ስራ መጀመሯ ይታወሳል፡፡

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 701 guests