ኢንተርኔትን፣ የድምጽና የፋክስ መልዕክትንና የስካይፒና ጎግል ቶክን መጠቀም የሚያስችል አዲስ አዋጅ ጸደቀ

  • PDF

አዲስ አበባ ሀምሌ 5/2004/ዋኢማ/- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 2ኛ አመት 1ኛ አስኳይ ጉባኤው ኢንተርኔትን መጠቀም የድምጽና የፋክስ መልዕክትን ወይም የስካይፒና ጎግል ቶክን መጠቀም የሚያስችል አዲስ አዋጅን አጸደቀ።

ይህ አዋጅ ቁጥር 761/2004 ተብሎ የጸደቀው አዲስ አዋጅ በ1994 ዓ.ም የወጣውንና የስካይፒ ተጠቃሚነትን ይከለክል የነበረውን ህግ ሙሉ በሙሉ እንዲሽር አድርጓል።

አዋጁ ከመጽደቁ በፊትም በሳይንስና መገናኛ ቴክኖሎጅ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና በውጭ መከላከያና ደህንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ውይይት ተደርጎበታል።

እንዲሁም የተለያዩ ባለድርሻ አካላትና የህብረተሰብ ክፍሎችም ከተወያዩበት በኋላ ማሻሻያ ተደርጎበት በትናንትናው እለት ጸድቋል።

የምክር ቤቱ አባላትም የቴሌኮም ማጭበርበር  መቆጣጠሪያ አዋጅ ላይ አስፈላጊ ነው ያሉትን ሃሳብ አንስተው ተወያይተውበታል።

የቴሌኮም ማጭበርበር ወንጀል ከቴሌኮም ኢንዱስትሪው ጋር እኩል እድሜ ያለው መሆኑና ከዚህ በፊት ህጉ የነበረ ቢሆንም ሀገሪቱ በዘርፉ ካላት እድገት ጋር  በሚመጣጠን መልኩ መሻሻል አለበት ብለዋል።

ከዚህ በፊት በዘርፉ የተሰማሩ ወንጀለኞችን ለህግ አቅርቦ ተጠያቂ ለማድረግ የህግ ክፍተት የነበረ ሲሆን፤  የአዋጁ መውጣትም የህጉን ክፍተት ለማስቀረት ያስችላል ተብሏል።

ከዚህ ቀደም አዋጁ ከቴሌኮም አገልግሎት አዋጅ ጋር ተቀላቅሎ የሚገኝ ስለነበርና አሁን ራሱን አስችሎ በማውጣት አፈጻጸሙን ለመከታተልና ለመተግበር አመች መሆኑን በጉባኤው ተመልክቷል።

የአዋጁ መጽደቅ በዚህ ወንጀል ለተሰማሩና ሊሰማሩ ላሰቡ ዜጎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ከማስቻሉም በላይ የረቀቀ የቴሌኮም ማጭበርበር የወንጀል ድርጊትን ለማስቆም ያስችላል መባሉን ኤፍቢሲ ዘግቧል።