በዓለም ታዳጊ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ይፋ ሆኑ
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዓለም ታዳጊ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ይፋ አደረገ።
ለ14ኛ ጊዜ ከሐምሌ 3 እስከ 8 ቀን 2004 ዓ.ም በስፔን ባርሴሎና በሚካሄደው የታዳጊ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን የሚወክሉ አስር ሴትና አስር ወንድ አትሌቶች ዝርዝር ይፋ ተደርጓል።
ፌዴሬሽኑ በ800፣ በ1 ሺህ 500፣ 3 ሺህ ቀጥታ፣ በ3 ሺህ መሰናክል፣ በ5 ሺህ እና በ10 ሺህ ሜትር የሚወዳደሩ አትሌቶች ምልመላ ያካሄደ ሲሆን፤ ቡድኑ ሰኔ 30 ቀን 2004 ዓ.ም ወደ ስፔን እንደሚጓዝ ተጠቁሟል።
በ800 ሜትር ሴቶች ዱረቲ ኢደኦና ዘይቱና ሙሐመድ፣ በወንዶች ጀና ዑመርና ፍቅር በለጠ ሲመረጡ፣ በ1ሺህ 500 ሜርት ሴቶች ሰንበሬ ተፈሪና ዓለም አምባዬ፣ በወንዶች ተሾመ ድሪብሳና የኔው ጠብቀው ተመርጠዋል።
በሶስት ሺህ ሜርት ሴቶች ሐፍታምነሽ ተስፋዬና ሕይወት ገብረኪዳን፣ በ3 ሺህ ሜርት መሰናክል ሴቶች ያብሥራ ቢተውና ጠጅነሽ ገቢሳ፣ በወንዶች አንሙት ምናሉና መረሳ ካህሳይ በውድድሩ ተካተዋል።
በ5 ሺህ ሜትር ሴቶች ቡዜ ድሪባና ሩቲ አጋ፣ በወንዶች ሙክታር ኢድሪስና ፀጋዬ መኮንን እንዲሁም በ10 ሺህ ወንዶች ይገረም ደመላሽና ክንዴ አጣናው ተመርጠዋል።
ሃያ ስድስት አባላትን ያካተተውን ቡድን የሚመሩት አቶ መአር አሊሴሮ ሲሆኑ አሰልጣኞች ግርማ ፈዬ፣ አብርሃም ኃይለማርያም፣ ንጋቱ ወርቁና እሸቱ ቱራ ናቸው።
በዓለም ታዳጊ ወጣቶች የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ወክለው የሚወዳደሩት አትሌቶች አዲስና ተተኪ ሊሆኑ እንደሚችሉ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኢዜአ ያደረሰው መግለጫ ያመለክታል።
| < Prev | Next > |
|---|


