የሰመራ ኤርፖርት ጥገና በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል

  • PDF

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2004/ዋኢማ - የሰመራ ኤርፖርት ደረጃውን የጠበቀ የበረራ አገልግሎት እንዲሰጥ በ10 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተደረገ ያለው ጥገና በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ እንደሚጠናቀቅ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ሲቪል አዬሽን ባለስልጣን በበኩሉ ወደ ኤርፖርቱ በረራ ከተጀመረ የቁጥጥር ስራውን ለመጀመር አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት የምህንድስና ዲዛይንና ግንባታ ቡድን መሪ አቶ አዘዘ በትሩ ለኢዜአ እንደተናገሩት የሰመራ ኤርፖርትን ለበረራ ዝግጁ ለማድረግ የሚያስችሉ ጥገናና መሰረተ ልማቱን የማሟላት ስራዎች ከሶስት እስከ አራት ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ።

በአሁኑ ወቅት የኤርፖርቱ የዙሪያ አጥርና የበረራ መቆጣጠሪያ ማማ ግንባታ ተጠናቋል።

በኤርፖርቱ የተገነባው ጊዜያዊ የመንገደኞች ማስተናገጃ ተርሚናል ህንጻ ግንባታ ተጠናቆ የመጀመሪያው ዙር ርክክብ ተፈጽሟል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበኩሉ ዓለም አቀፍ በረራን ከማስፋት ጎን ለጎን ለአገር ውስጥ የበረራ አገልግሎትን በጥራትና በሽፋን ለማሳደግን ትኩረት መስጠቱን ገልጿል።

የአየር መንገዱ የህዝብ ግንኙነት አገልግሎት የሰመራ ኤርፖርት ለአገልግሎት ዝግጁ ከሆነ በማንኛውም ጊዜ አዲስ በረራ ለመጀመር ዝግጁ መሆኑን አስታውቋል።

አየር መንገዱ ወደ ሰመራ በሣምንት ለሶስት ቀናት በረራውን ለማካሄድ ማቀዱንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአሁኑ ወቅት በአገር ውስጥ ከሚጠቀምባቸው 8 ቦምባርዴር ኪው 400 አውሮፕላኖች በተጨማሪ ተመሳሳይ አቅም ያላቸው አምስት ዘመናዊ አውሮፕላኖችን በዚህ ዓመት ወደ አገር ውስጥ እንደሚገቡ አመልክቷል።

አትራፊ የሆኑ የአገር ውስጥ የበረራ መስመሮች ላይም የበረራ ቁጥር በመጨመር አቅርቦቱን እንደሚያሳደግም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው እንዳሉት የሰመራ ኤርፖርት በረራ የሚጀምር ከሆነ ባለስልጣኑ አስፈላጊውን የቁጥጥርና የክትትል ስራ በአፋጣኝ ለመጀመር የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቋል።


  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 375 guests