በኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የመጠቀም ፍላጎታቸው ላልተሟላ ዜጎች አዲስ አቅጣጫ ተዘረጋ

  • PDF

አዲስ አበባ ሰኔ 28/2004/ዋኢማ/ - ባለፉት ዓመታት የስነ-ተዋልዶ ጤናን ለሁሉም ተደራሽ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት አመርቂ ውጤት መመዝገቡን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከሰተብርሃን አድማሱ ገለፁ።

በኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት ለመጠቀም ፈልገው ፍላጎታቸው ያልተሟሉ ዜጎች 25 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፤ ይህን ክፍተት ለመሙላት አዲስ አቅጣጫ መዘርጋቱን ዶክተር ከሰተ ብርሃን ተናግረዋል፡፡

ይህም በኢትዮጵያ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት የመጠቀም ፍላጎታቸው ላልተሟላ ዜጎች አዲስ አቅጣጫ በመዘርጋት በኩል ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ በዓመት በ2 ነጥብ 6 በመቶ እንደሚያድግ የ2003 የስነ-ህዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት የሚያመለክተው፤ ይህ እድገት አሁን ባለበት የሚቀጥል ከሆነ ሃያ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የሀገሪቱ ህዝብ ከአንድ መቶ ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ ነው የሚጠበቀው፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር ከምጣኔ ሃብት ሁኔታው ጋር እንዲራመድ ለማድረግ ደግሞ የስነ-ህዝብ ፖለሲ ቀረጻ ተግባራዊ በመደረግ ላይ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ በጋብቻ ላይ ካሉ አራት ሴቶች መካከል ከአንድ በላይ የሚሆኑት ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ ዘዴ የሚጠቀሙ ሲሆን፤ በአጠቃላይ ከአንድ በላይ ዘመናዊ የወሊድ መቆጣጠሪያ የሚጠቀሙት ደግሞ በአምስት አመት ውስጥ አሃዛቸው በእጥፍ አድጎ 29 በመቶ ላይ ደርሷል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስነ-ህዝብ ፈንድ ተወካይ ዶክተር ቤንዋ ካላሣ ኢትዮጵያ ዘመናዊ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎትን ከማስፋፋት ጎን ለጎን በዘርፉ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመሙላት ጥረት ማድረግ አለባት ብለዋል፡፡

ከውጤቱ ባሻገር ተግዳሮች አሉብን ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በማህበረሰቡ መካከል በአጠቃቀም ረገድ ክፍተት መኖሩንና የአቅርቦት እጥረትና የገንዘብ ክፍተት ደግሞ ዋነኞቹ ሲሆኑ እነዚህን መሙላት ይጠበቅብናል ብለዋል።

በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የስነ-ህዝብ ጉዳይ ዳይሬክተር ወይዘሮ ገነት መንግስቱ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለውን መጠነ ሰፊ የልማት ስራ ከዳር ለማድረስ የህዝብ ቁጥሩን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ ቀርፃለች ብለዋል፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የኢትዮጵያ ህዝብ ቁጥር አሁን ባለበት የሚጨምር ከሆነ ሃያ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ5 ሚሊዮን በላይ አዲስ የስራ እድል መፈጠር ይኖርበታል ሲል የዘገበው የኢሬቴድ።


  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 186 guests