በከተማው እየተካሄደ ባለው የመልሶ ማልማት ሥራ የህዝቡ ተሳትፎና ግንዛቤ አበረታች መሆኑ ተገለፀ
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2004/ዋኢማ/ የአዲስ አበባ ከተማን ገፅታ ለመቀየር በሚከናወነው የመልሶ ማልማት ሥራዎች ላይ የህዝቡ የነቃና አበረታች ተሳትፎ እያደረገ መሆኑን በአዲስ አበባ መስተዳድር በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ ተገለጸ።
ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ከአዲስ አበባ መስተዳድር ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ መልሶ ማልማት እንቅስቃሴ ላይ ባካሄደው የሕዝብ አስተያየት ጥናት የከተማዋ ነዋሪዎች በተለያዩ ሥፍራዎች እየተከናወኑ በሚገኙት የመልሶ ማልማት ሥራዎች ላይ ያላቸው የግንዛቤ ደረጃና የሚያደርጉት ተሳትፎ የላቀ ነው።
በጥናቱ ከ3ሺ በላይ ነዋሪዎች እንደተሳተፉና ከእነዚህ ውስጥ 75 በመቶ የሚሆኑት የጥናቱ ተሳተፊዎች በከተማው በተካሄዱት የመልሶ ማልማት ሥራዎች የተካተቱ መሆናቸውን በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በጥናትና የህዝብ ግንኙነት ስራዎች መመሪያ የህዝብ አስተያየት ጥናት ዋና ክፍል የጥናት አደራጅና ትንተና ከፍተኛ ባለሙያ አቶ አበራ ገብረኪዳን ገልፀዋል።
በጥናቱ አስተያየታቸውን ከሰጡት ሰዎች መካከል 79 በመቶ የሚሆኑት በመልሶ ልማቱ ከመኖሪያ ቦታቸው ለመነሳት ፍቃደኛ የሆኑ ሲሆን፤ 65 በመቶው ደግሞ በልማቱ ምክንያት ወደ ሌላ ቦታ ከተዘዋወሩ በኋላ ሕይወታቸው ለውጥ እንዳመጣ ገልፀዋል።
የጥናቱ ተሳታፊዎች ከሆኑት የ89 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ስለ ከተማዋ መልሶ ማልማት ጥሩ ግንዛቤ እንዳላቸው ጥናቱ ያሳያል በማለት አቶ አበራ ተናግረዋል።
በውይይቱ ወቅት አስተያየታቸውን የሰጡት አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ መንግሥት በህብረተሰቡ ውስጥ የፈጠረው መልካም መነቃቃት ትልቅ የልማት ግብአት እንደሆነና በመልሶ ማልማቱ ሥራ ላይ እንደዚህ አይነት ተከታታይ ውይይቶች መደረጋቸው ችግሮችን በጋራ ለመፈታት እንደሚያገዙ ገልጸዋል።
በልማቱ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙ የተለያዩ ችግሮችን የውይይት ተሳታፊዎቹ ያነሱ ሲሆን፤ የግል ይዞታ ለነበራቸው የልማት ተነሺዎች በአስተዳደሩ የሚሰራው የካሳ ልኬት ወቅታዊ ሁኔታውን ያላማከለና መጓተት እንደሚያሳይ መሆኑን በመጥቀስ መመሪያው በሚያዘው የመግባቢያ ሰነድ አማካኝነት ጉዳዮች ሊፈጸሙ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የመሬት ባንክና አስተዳደር ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ግርማ በበኩላቸው፤ የከተማጀው አስተዳደር በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቅረፍ በ2002 ዓ.ም የወጣውን መመሪያ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማካሄድ አስተያየቶችን በማካተት ተሻሽሎ እንዲወጣ ከመደርጉም በላይ መመሪያውን ህዝቡ እንዲያውቀው በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ተደርጓል።
የምልሶ ማልማቱ ሥራ ሙሉ ለሙሉ ከችግር የፀዳ እንዳልሆነ የተናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ወይዘሮ ፍሬህይወት አያሌው ችግሮቹን ለመፍታት ህብረተሰቡ ከመንግሥት ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባው አሳስበው፤ ይህም የተያዘውን ልማት ይበልጥ ውጤታማ ያደርገዋል ብለዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


