የስነ-ምድር መረጃ ሽፋንን ለማሳደግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ገለፀ
አዲስ አበባ ሰኔ 27/2004/ዋኢማ/ - የሥነ-ምድር መረጃን በጥራትና በስፋት በማመንጨትና ለተጠቃሚ በማቅርብ የዘርፉ ሽፋንን በአማካኝ 80 በመቶ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ስለሚሰራቸው ሥራዎችና ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች ከዘርፉ ተገልጋዮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ያካሄደውን የውይይት መድረክ የማዕድን ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ቶሎሳ ሻጊ ሲከፍቱ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ለዕቅዱ ስኬት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የማፋጠን ተልዕኮ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።
ለዕቅዱ ስኬትና ድህነትን ለመለወጥ ሰርቬዩን የሥነ-ምድር መረጃን በጥራትና በስፋት በማመንጨትና ለተጠቃሚ በማቅርብ የሥነ-ምድር መረጃ ሽፋንን በአማካኝ 80 በመቶ ለማሳደግ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዘርፍ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም የማዕድን ሃብቶች የውጭ ምንዛሪ አስተዋዖኦ በ10 እጥፍ ማሳደግና ኢንዱስትሪ ልማት የጀርባ አጥንት እንዲሆን የማድረግ ራዕይ ይዛ በመንቀሳቀስ ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በስነ-ምድር ጥናት ዘርፍ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መሠረታዊ የጂኦሳይንስ ካርታ ዝግጅት፣ የማዕድን ፍለጋና ክምችት ግምት፣ የከርሰ ምድር ውሃ ሃብት ጥናት፣ የጂኦተርማል ሃብት ጥናትና የሥነ-ምድር አደጋዎች ጥናት መሆናቸውን አብራርተዋል።
የጂኦሳይንስ መረጃዎች በመሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ ግቦች ተቀርፆላቸው ከምንጊዜውም በላይ ለተጠቃሚ በማቅርብ ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ዋና ዳይሬክተር አቶ ማስረሻ ገብረሥላሴ በበኩላቸው፤ ለእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ስኬት ጠንክሮ መስራት ሁሉም ዜጋ የድርሻውን መወጣት እንደሚጠበቅበት ገልፀዋል።
ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር ለመግባት በምታደርገው ጥረት መረጃን በማቅርብ ረገድ የሥነ-ምድር ባለሙያዎች የበኩላቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸውም አሳስበዋል።
የውይይቱ ዓላማ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የሚያከናውናቸውን ተግባር ለዘርፉ ተገልጋዮችና ለባለድሻ አካላት ከማሳወቅ በተጨማሪ የጂኦ ሳይንስ ጥናትና መረጃዎች በጥራት በዓይነትና በመጠን ለማሻሻል የሚደረገው ጥረት ግብዓት ለማሰባሰብ ጠቀሜታ እንዳለው መናገራቸውን የዘገበው የኢዜአ ነው።
| < Prev | Next > |
|---|


