ስውር ዓላማ ላላቸው ቡድኖች ፈረስ ላለመሆን
ኢብሳ ነመራ
ከያዝነው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ተፈጥሮ የነበረው ጉዳይ የሃይማኖቱ ተከታይ ያልሆኑ ዜጎችንም ትኩረት ስቦ ከርሟል። የጉዳዩ መነሻ በዋናነት ሶስት ጥያቄዎች ላይ ያተኮረ እንደነበረም እናስታውሳለን።
እነዚህም ቀደም ሲል የነበረውን የእስልምና ጉዳይ ም/ቤት (መጅሊስ) የሚተካ ም/ቤት አባላት ምርጫ ይካሄድ፣ አወሊያ የተባለው ተቋም ህዝበ ሙስሊሙ በመረጠው ቦርድ ይመራ እንዲሁም አልሀበሽ የተባለውን የእስልምና አስተምህሮ በግዳጅ መስጠት ይቁም የሚሉ ነበሩ።
እነዚህን ጥያቄዎች ለማስፈፀምም መፍትሄ አፈላላጊ ጊዜያዊ ኮሚቴ መሰየሙም ይታወሳል፡፡ ከላይ የተገለፁት ሶስት ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ መንግስትን የማይመለከት ቢሆንም መንግስት ምላሽ እንዲሰጥበትም ጥያቄ ቀረበ፡፡ መንገስት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ህገመንግስታዊ ስልጣን እንደሌለው እየታወቀ ጉዳዩ ለመንግስት መቅረቡ ብዙዎችን ግራ አጋብቶ ነበር።
የሆነ ሆኖ በአንድ ወገን መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ዘንድ ትኩሳት ፈጥሮ የነበረውን ይህን ጥያቄ “መንግስት ካላየልኝ” ብሎ ድርቅ በማለቱ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በሰላም ሃይማኖቱን የመከተል፣ የአምልኮ ስርዓቱን የመፈፀም መብት ስላለው፣ ይህ ተግባራዊ ይሆን ዘንድ በማሰብ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ጥያቄዎቹን ተቀብሎ ከኮሚቴው ጋር ተወያይቶ በጉዳዩ ላይ እልባት ያስገኛል ያላቸውን መፍትሄዎች አስቀምጧል፡፡
ይህም ሙስሊሙ ህብረተሰብ የሃይማኖት መሪዎቹን የመምረጥ መብትና ነፃነት ያለው መሆኑን ከግንዛቤ በማስገባት የመጅሊሱ ምርጫ እንዲካሄድ የሚለው ቀዳሚው ነው፡፡ በግዳጅ የተሰጠ የተባለውን አስተምህሮ በተመለከተ፣ ማንም በሌላው ላይ እምነቱነና አመለካከቱን በሌሎች ላይ በግዳጅ መጫን እንደማይችል መነሻ በማድረግ፣ አልሀበሽ የተባለውን አስተምህሮ በግዳጅ የሰጠ አለመኖሩ፣ ሆኖም የሃይማኖቱ መሪዎች ተገቢ ነው ብልው ያመኑትን አስተምህሮ ብቃቱ አላቸው ብለው ባመኑባቸው መምህራን ማስተማር እንደሚችሉ ይህ ጉዳይ በፍፁም መንግስትን እንደማይመለከት ተገልፆ ነበር፡፡
ህዝበ ሙስሊሙም በራሱ ውሳኔ የመረጠውን አስተምህሮ የመቀበል፣ የመማር መብት ያለው መሆኑንና ይህም ህገመንግስታዊ መብት እንደሆነ አፅንኦት ተሰጥቶት እንድነብርም ይታወሳል፡፡ በሶስተኝነት የአወሊያን ተቋም በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ሙስሊሙ ህብረተሰብ መርጦ በሚሰይመው ቦርድ መተዳደሩ ተገቢ ነው የሚል መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበረም እናስታውሳለን።
አሁን በስራ ላይ ያለው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ም/ቤትም (መጂሊሥ) በዚሁ በውይይት በተደረሰበት ጉዳይ ላይ መስማማቱን ገልፆ፣ ወደማስፈፀም እንደሚገባ አሳወቀ።
ይሁን እንጂ የሙስሊሙን ጥያቄ ለማቅረብ ውክልና አለኝ ያለው ኮሚቴ በውይይቱ የተደረሰበት መግባባት ተግባራዊ ይሆን ዘንድ ከመከታተል ይልቅ፣ የፈጠረው ትኩሳቱ ሞቀው መሰለኝ ሆይ ሆይታውን ቀጠለበት፡፡ በተለይ ሙቀት አለ ብሎ በገመተበት አካባቢ እሳት ይቀጣጠል ዘንድ ማራገብን ስራዬ ብሎ መያያዙን ስራው በገሃድ የሚያሳብቅበት የአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛ ፕሮግራም ጋር ሆነው መሬት ላይ የሌለውን ጉዳይ በሬዲዮ ሞገድ ማጋጋሉን ተያያዙት። በአገር ውስጥ ያሉ በተለይ የሙስሊሞች ጉዳይ ላይ የሚያተኩሩ ጥቂት ጋዜጦችም የህዝበ ሙስሊሙን ቀልብ ለመናጥ መቀበጣጠራቸውን ተያያዙት።
የሞስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ የተባለው ቡድን በዋናነት አንስቶት የነበረው የመጅሊስ ምርጫ መካሄዱ ቁርጥ ሆኖ ዝግጅት ሲጀመር፣ የምርጫው መካሄድ እንዳልጣመው የሚያመላክቱ አዳዲስ ጥያቄዎችን ማንሳት ጀመረ። ቀደም ሲል ህዝበ ሙስሊሙን የሚወክል መጅሊስ በነፃ ምርጫ ይመስረት የሚለው ጥያቄ፣ ያልነበረውን ቀንድ አወጥቶ ብቅ አለ። ምርጫው በቀበሌ/ ወረዳ ሳይሆን በመስጂድ ይካሄድ የሚል ነው።
እዚህ ላይ ዋናው ጉዳይ ሙስሊሙ ህብረተሰብ ወኪሎቹን መምረጡ ሆኖ ሳለ፣ ከዚህ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የእስልምና ጉዳዮች ም/ቤት አባላት በቀበሌ/ወረዳ ይመረጡ የነበረ መሆኑ፣ ኮሚቴው “የለም ይህን አልፈልግም” የሚለው ተቀፅላ መነሳቱን ስንሰማ “ኮሚቴው ስውር አጀንዳ አለው፣ አለያም የተለየ አጀንዳ ባላቸው ሰዎች እየተመራ” ነው የሚል ጥርጣሬ አድሮብናል።
“አንድ ሃገር አንድ ሃይማኖት፣ ኢትዮጵያ የክርስቲያን ደሴት ናት” እያለ ድሮ ከላያችን ላይ ካራገፍነው የበሰበሰ አቋም ጀርባ ያለው፣ ደርግ ሲወድቅ ከሃይማኖት መሪነት ይልቅ ኢሰፓነታቸው ያየለ ስለነበረ፣ መንግስቱ ሃይለማርያም ቤተመንግስቱን ለቆ ሲፈረጥጥ፣ አገር ጥለው ከፈረጠጡት ዙሪያ የተሰበሰቡትና ራሳቸውን “ስደተኛው ሲኖዶስ” ብለው የሚጠሩት ሰዎች፣ እንዲሁም በአሜሪካና አውሮፓ ማክዶናልዳቸውን እየገመጡ “ታጋዮች ነን” የሚሉ ጥቂት ግለሰቦችን የያዘው የግንቦት 7 ቡድን ወደ ኮሚቴው ጠጋ ጠጋ ማለቱን ስንሰማ ደግሞ የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ የተባለው ኮሚቴ ሌላ አጀንዳ አለው የሚለው ጥርጣሬያችን የበለጠ እንዲያይል ምክንያት ሆኗል።
ቀደም ሲል ህገመንግስታዊውን ስርዓት በአገር ውስጥ ሆነው በነፃ ፕሬስ ከለላ ለመገዝገዝ ሲፍጨረጨር የነበረው፣ በናፋቂ ደርግ አቋሙ የሚታወቀው የአፍሪካ ቀንድ ይባል የነበረ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ በኋላም በ1997 በሙስሊሙ ውስጥ ግጭት ለመፍጠር ከተንቀሳቀሰው ቡድን ጋር ባለው ተሳትፎ በፍ/ቤት የቅጣት ውሳኔ ተላልፎበት ቅጣቱን ጨርሶ የወጣው አደም ከሚል የተባለ ግለሰብ እንዲሁም የኢህአዴግ አባል የነበረና የባህርዳር ከተማ ከንቲባ የነበረውና በስራ ድክመት ከኢህአዴግ አባልነቱና ከከንቲባነቱ የተሰናበተው አስማማው ዩሱፍና መሰል ስብዕና ያላቸው ግለሰቦች በፖለቲካ ካባቸው ላይ ጣቂያ ደርበው የሰሞኑን ትኩሳት መቆስቆሳቸውም እንዲሁ ጥርጣሬያችን እንዲያይል አድርጎታል፡፡
ቀደም ሲል እንዳነሳሁት መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴው “መጅሊሱ በነፃ ምርጫ ይመረጥ” በሚል መግባባት የተደረሰበት ጉዳይ ላይ አዲስ ቅጥያ ይዞ ከመምጣቱ ጋር ሌላም የታዘብነው ነገር አለ፡፡ ይህም ሊካሄድ በዝግጅት ላይ ያለውን የመጅሊስ ምርጫ ከወዲሁ “መጨበርበሩ አይቀሬ ነው” የሚል አንደምታ ያለው ወሬ ማናፈስ መጀመሩ ነው፡፡
ይህ አካሄድ ከምርጫ 97 በፊት የነበረውን የቀድሞውን ቅንጅት አካሄድ ያስታውሰናል፡፡ የቀድሞው ቅንጅት የ97ቱ ምርጫ ከመካሄዱ ከወራት በፊት ለአባላቱና ደጋፊዎቹ “ምርጫው መጭበርበሩ አይቀርም” የሚል ወሬ መንዛቱን እናስታውሳለን፡፡ በኋላም የምርጫው ውጤት ይፋ ሆኖ በፌደራልና ከአ/አ በስተቀር በተወዳደረባቸው የክልል ም/ቤቶች ውስጥ አለማሸነፉን ሲያውቅ “ይሄው እንዳልኩዋችሁ ምርጫው ተጭበረበረ” ብሎ መንግስትን በኃይል ከመጣል ውጭ አማራጭ እንዳልነበር ነግሮ ሁከት ቀስቅሷል፡፡
በዚህ ግፊት በአንዳንድ የአገሪቱ ከተማዎች ውስጥ በተካሄደ ሁከት፣ ጥቂት የዋህ ንፁሃን ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል፣ አካላቸው ጎድልዋል፡፡ ቅንጅት በኃይል ስልጣን የመያዝ ሕልሙን ለማሳካት ማግዷቸዋል፡፡
በሙስሊሙ ማህበረሰብ ተወክያለሁ የሚለው ኮሚቴ - በቅድሚያ ይዞት የተነሳው ጥያቄ እልባት ካገኘ በኋላ ቅጥያ ጥያቄዎችን እያነሳ ትኩሳት እየፈጠረ እድሜውን ማራዘም መፈለጉ፣ አንዳንድ ግለሶቦች የፖለቲካ ካባቸውን እያወለቁ ጣቂያ አጥልቀው በአጃቢነት ከጎኑ መሰለፋቸውና ገና ያልተካሄደው የመጅሊስ ምርጫ “መጭበርበሩ አይቀርም” የሚል የቀድሞውን ቅንጅት የውዥንብር ፈጠራ ስልት መከተላቸው፣ የሁከት አማራጭን በመከተል ለዓላማቸው መሳካት የዋሁን ወጣት ሙስሊም ሊማግዱ መዘጋጀታቸውን ያመለክታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አጀንዳቸው የነጠረ ኃይማኖታዊ ሳይሆን ኃይማኖት የተቀባ ፖለቲካ መሆኑንም ይጠቁማል፡፡
አሁን ሙስሊሙ ወክሎኛል የሚለው ኮሚቴ፣ የቀድሞው ቅንጅት “ምርጫ መጭበርበሩ አይቀርም” ወሬን መሰረት ያደረገ የአመፅ መንገድ ሲያዘጋጅ ብዙ ተመክሮ ተዘክሮ ለድርድርም ለሽምግልናም አልገዛ ብሎ እንደነበር ሊያስታውስ ይገባዋል፡፡ የቀድሞው ቅንጅት በማንአለብኝነትና በእብሪት የተከተለው መንገድ ለየዋህ ንፁሃን ዜጎች የሕይወት መጥፋት ምክንያት መሆኑ አሳዛኝ ቢሆንም፣ አመራሮቹ ኋላ ላይ በሕገወጥነት ቃሊቲ ገብተው በፍ/ቤት ክርክር ላይ ተረተዋል ፡፡
ሙስሊሙ ህብረተሰብ በተለይ ተቆርቋሪ መስለው ስውርና ይፋ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች መቀላቀላቸውን፣ አወቅላቹኋለሁ ከሚለው ኮሚቴ አካሄድ ጋር አጢኖ የጉዳዩ ባለቤት እኔ ነኝና ቀናውንና ሰላማዊውን መንገድ ያዙ ሊላቸው ይገባል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የደርግ ስርአት ከተገረሰሰ በኋላ ባሉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ ብቻ ከ60 ሺህ በላይ መስጂዶች መገንባታቸው ይታወቃል፡፡ ይህም ባለፉት ስርአቶች ሲገፉ የቆዩት ሙስሊም ኢትዮጰያዊያን ሃይማኖታቸውን በነፃነት የመከተል፣ በሰላማዊ መንገድ የማስፋፋትና የአምልኮ ስርአታቸውን የመክወን መብትና ነፃነታቸው በሕገ ምንግስቱ መሰረት መከበሩን ያረጋግጣል፡፡ በስልጣን ላይ ያለውም ምንግስት ለሕገ ምንግስቱ ተግባራዊነት ያለውን ቁርጠኝነት በግልፅ ያሳያል፡፡
እንግዲህ ይህን መንግስት ነው በእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ጫና አሳድሯል በሚል አንዳንድ ወገኖች ለመውቀስና ለማስወቀስ እይሞከሩ የሚገኙት፡፡ ክእነዚህ አሁን መንግስትን ለመውቀስና ለወቃሽ አሳልፎ ለመስጠት እየተራወጡ ከሚገኙ ግለሰቦችና ቡድኖች መሃከልም በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ በርካታ መስጊዶች ከመሰራታቸው ጋር በተያያዘ “መንግስት የክርስትና ሃይማኖትን በማዳከም እስልምና እንዲስፋፋ እየሰራ ነው” ብለው መሰረተ ቢስ ወሬ በማውራት በክርስቲያን ምዕምናን ዘንድ ጥርጣሬ እንዲነግሥ ለማድረግ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችም ይገኙበታል፡፡
በሃይማኖት፣ በብሄር፣ በአመለካከት፣ … እኩልነትና ነፃነት የማያምኑ በመሆኑም የእነዚህን መብቶችና ነፃነቶች መከበር ያረጋገጠውን ሕገ መንግስት ለመናድ አንዳች ተኣምር በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ ወገኖች በሙሉ፣ ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን በመጣላቸው ሕገ መንግስት ላይ ይነሳሉ ብለው ቋምጠዋል፡፡
የዚህ አይነት አካሄዶች በቅንነት ለሙስሊሙ ከመቆርቆር የመነጩ አለመሆናቸውን ሙስሊም ኢትዮጵያዊያን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡ “ጅብ ጥንብ አለ ቢሉት አቅጣጫ ሳይጠይቅ ሮጠ” እንዲሉ፣ አመፅ ይቀሰቅሳል ብልው የገመቱትን ጉዳይ በሙሉ ለቀም አድርገው ሕዝብን በመንግስት ላይ ለመቀስቀሻ ፍጆታነት ለማዋል ያቆበቆቡ ቡድኖች አካሄድ መሆኑንም ሊያስተውል ይገባል፡፡
የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ በሚል ስያሜ የተቋቋመው ኮሚቴም ቅን ከሆነ “ሆይ ሆይ” እያለ የሚያሟሙቅ ሁሉ፣ ለሙስሊሙ መብትና ነፃነት የቆመ አለመሆኑን ልብ ሊል ይገባለ፡፡ ይህ ካልሆነ የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው ቡድኖች የሚጋልቡት መድረሻውን የማያውቅ ፈረስ የመሆን አደጋ ከፊቱ ይጠብቀዋል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


