……ግመሎቹ ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል!

  • PDF

ቤተልሔም ሸዋንግዛው

በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ከሚገኙት የዓለም አገራት መካከል ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ምንም እንኳ ይህን ለውጥ ለማረጋገጥ ከእኛ የአገሪቱ ዜጎች የቀረበ አለ ባይባልም ዓለም አቀፍ ተቋማትም ሆኑ የተለያዩ የምጣኔ ኃብት ተመራማሪዎች ያለውን ሁኔታ በሳይንሳዊ መንገድ በመቃኘት፣ በመመርመርና በማስተንተን እውነትም አገሪቱ በሚያስደንቅ የለውጥ ጎዳና ውስጥ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡ የተለያዩ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም የጥናት ውጤቶቹንና የራሳቸውን ምልከታ በማድረግ እውነቱን በየጊዜው ለዓለም በመዘገብ ላይ ናቸው፡፡

በተለይ ካለፉት ሶስት ዓመታት ወዲህ በሚነሱ አጠቃላይ የዓለም ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ አገራችን በመልካም ጎኑ ሳትጠቀስ ያለፈችበት አጋጣሚ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር ካለፈው 2011 ጀምሮ እስካሁን ድረስ በዓለም የምጣኔ ኃብት ጉዳዮች የወጡትን ሪፖርቶች ለአብነት በዓለም ደራጃ ሰፊ ተቀባይነት ያላቸውን ጥቂቶቹን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም፣ የዓለም ባንክ፣ Economist Intelligence Unit፣ መቀመጫውን እንግሊዝ ያደረገው የምጣኔ ኃብት ምርምር ድርጅት አርነስና ያንግ እንደዚሁም Global Economic Prospects፣ Carnegie Endowment for International Peace የተሰኘው ተቋምና African Economic Outlook ባለፉት አስር ወራቶች ጊዜ ውስጥ ያወጧቸው ዘገባዎች ኢትዮጵያ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት እያሳየች ያለች አገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡
ለቁጥር የሚታክቱ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃንም ወደኢትዮጵያ መጥተው ሁኔታውን በአካል በመመልከት፣ የተለያዩ በልማቱ ዘርፍ የተሰማሩ ባለኃብቶችን፣ የአገሪቱ ዜጎችን፣ ገለልተኛ ናቸው የሚባሉ የልማት ተመራማሪዎችንና የሚመለከታቸውን የመንግስት የስራ ኃላፊዎችን ዋቢ በማድረግ እንዲሁም የራሳቸውን ሙያዊ ምልከታ በማከል በተለያየ መልኩ የትንታኔ ዘገባዎችን፣ ዶኩመንተሪ ፕሮግራሞችንና የገፅታ ዘገባዎችን አቅርበዋል፡፡
እነዚህ አካላት እየገለፁ ያለው እውነት ኢትዮጵያ በፈጣን እድገት ውስጥ መሆኗን ብቻ አይደለም፡፡ አገራችን እያሳየችው የሚገኘው የለውጥ መንገድ ከዓለም አገራት ሁሉ የላቀና እጅግ ውጤታማ መሆኑንም በማድነቅ ጭምር ነው፡፡ በመጪዎቹ ዓመታት የኢትዮያ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት መሪነቱን የያዙትን ቻይናና ህንድን ጭምር ሊቀድም እንደሚችልም እላይ በተጠቀሱት ሪፖርቶች ላይ ተንብዮዋል፡፡

እነዚህ አካላት አክለውም አገሪቱ በዚህ የለውጥ ጎዳና በዚሁ ፍጥነት የምትቀጥል ከሆነም በእርግጥም ዜጎቿ ከድህነት እንደሚወጡ፤ ከተመፅዋችነትም የሚላቀቁ መሆኑን አመላክተዋል፤ ኢኮኖሚውን ለዚህ ለውጥ ያበቃው ፖሊሲና ስትራቴጂም እጅግ ተስፋ የሚጣልበት በመሆኑ ለሌሎች የአፍሪካ አገራትም ምሳሌ ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ትንታኔዎችንም አቅርበዋል፡፡ 

ይህ በአገራችን ታሪክ ያልታየ ክስሰት በዋናነት ዜጎችን ከከፋ ድህነት በማውጣት በደስታ የተሞላ ህይወትን የሚያጎናፅፍ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህ  እንደተጠበቀ ሆኖ አዲሱ የለውጥ ምእራፍ የዜጎችን የስነ ልቦና ውድቀት በመቀልበስ መንፈሳዊ መነቃቃትን ማምጣትን ጨምሮ ለእድገት ጎዳናው ኃይል የሚሆኑ ሌሎች የሚያመረቁ ትሩፋቶችም እያስገኘ መሆኑን በርካታ አብነቶችን አንስቶ መነጋገር ይቻላል፡፡

አገራዊ እድገታችን ከ20 ዓመታት በፊት በሚያሳፍር ድህነት ብቻ እንጠራ ለነበርነው እኛ ኢትዮጵያን እንደገና እንደመወለድ ይቆጠራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከዚህም በላይ ይህ አሁን በአገራችን የሚታየው ተስፋ የሚጣልበት የለውጥ መንገድ ዜጎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አገራቸውን እንዲወዱ፤ በአገራቸው ላይ የበለጠ ተስፋ እንዲጥሉ የሚያደርጋቸው መሆኑም ግልፅ ነው፡፡

ከዚህ ነጠላ እውነት ጋር በተያያዘ የተለያዩ አብነቶችን ማንሳት የሚቻል ቢሆንም አንዱን ብቻ ጠቅሼ ልለፍ፡፡ 

ከዚህ በፊት አገራቸውን ለስም ከመጠቀም ባለፈ ብዙም ተስፋ ይጥሉባት ያልነበሩ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ዜጎች በአሁኑ ወቅት አገራቸውን መምረጥ ጀምረዋል፡፡ በአገሪቱ እየታየ ባለው ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ በመማረክ እውቀታቸውንና ኃብታቸውን በመጠቀም በአገራቸው ለመስራት በመነሳሳት ላይ ናቸው፡፡ 

እነዚህ ዜጎች እንደ አውሮፓ አቆጣጠር እስከ ኃምሌ 2011 ድረስ ብቻ በጠቅላላው 20 ቢሊዮን ብር የሚገመት መዋእለንያው በአገራቸው በማፍሰስ ራሳቸውን፣ አገራቸውንና ወገናቸውን በሚጠቅሙ የተለያዩ የልማት ዘርፎች ተሰማርተዋል፡፡  እነዚሁ ወገኖቻችን በተጨማሪም ወደአገራቸው የሚልኩት የውጭ ምንዛሪ መጠንም ከጊዜ ወደጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ይገኛል፡፡

በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ2010 ብቻ በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ብለው በህጋዊ መንገድ ወደአገር ቤት የላኩት የውጭ ምንዛሪ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚልቅ ከአንድ የዜና አውታር አድምጫለሁ፡፡ 

ይህ የአገራችን አዲስ የለውጥ ጎዳና ሌላ አብይ ሚናም እየተጫወተ ነው፡፡ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ዜሮ ኢኮኖሚ በነበረባት አገራችን በአጭር ጊዜ ብቻ እንዲህ የሚታይና የሚጨበጥ እድገት መመዝገቡ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ጭምር መሳቡም አልቀረም፡፡

እናም እየታየ ያለው ለውጥ ለአገር እድገት መቀላጠፍ፣ ለቴክኖሊጂና እውቀት ሽግግር ብሎም የወጪ ንግድን ለማጠናከርና ሰፊ የስራ እድልን ለመፍጠር አንዱና ወሳኝ የሆነውን ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የበለጠ ማጎልበት ተችሏል፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በቅርቡ ይፋ የሆነውና “Doing Business 2012” የተሰኘው የዓለም ባንክ ሪፖርት ኢትዮያ ለኢንቨስትመንትና ሌሎች ስራዎች አመችነቷ እያደገ መምጣቱን አረጋግጧል፡፡ የዓለም ባንክ ይህ ጥናት የሚያሳየው በአገሪቱ አዋጭ የሆነ የኢኮኖሚ እንቀስቃሴ እየተፈጠረ መሆኑን ነው፡፡

በዚህም የተነሳ ግዙፍ የሚባሉትን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መስራት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች በአገሪቱ ያፈሰሱት መዋእለንዋይ በመቶ ቢሊዮኖች ብር የሚገመት ነው፡፡ 

ይህ ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እድገት ያለማቋረጥ ቀጥሏል፡፡ በየእለቱ የምናደምጣቸውም ሆኑ የምናነባቸው የመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች በአገራችን አዳዲስ ኩባንያዎች እየተከፈቱ፤ ሌሎችም ጥያቄ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን ነው፡፡

አዎንታዊው የለውጥ ጎዳናው የወለደው ነው ብዬ የማምነው ሌላው መልካም ነገር አገራችን በዓለም ጎብኚዎች የትኩረት ዓይን ውስጥ የመግባቷ ጉዳይ ነው፡፡ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ የቱሪስት መስህብ ኃብት ያላት አገር ብትሆንም የአገሪቱ ያላትን የማስተዋወቅ አቅም ማነስን ጨምሮ በተለያዩ ምክንያቶች ተገቢውን ጥቅምም ሆነ ትኩረት ሳታገኝ ስለመቆየቷ አብነት ማንሳት የሚያሻ አይመስለኝም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን በተለይ ካለፉት አስር ዓመታት ወዲህ አገሪቱ የዓለም አቀፍ ቱሪስቶች ትኩረት ሆናለች፡፡ በዚህም ምክንያት ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከመቼውም ጊዜ እጅግ በላቀ መልኩ እየጨመረ ይገኛል፡፡

ከዚሁ ጋርም አገራችን በተለይ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ የዓለም ኢኮኖሚና ፖለቲካ ጉዳዮች የሚመከሩባቸውን ዓለም አቀፍ  ጉባኤዎችን እንድታስተናግድ ተመራጭ መሆን መጀመሯን ማንሳቱ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

አገሪቱ ተመራጭ የሆነችው ኢኮኖሚው አቅም የፈጠረላት መሆኑ በመረጋገጡ ጭምር ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አገሪቱ በቅርቡ በአንድ ጊዜ ከሶስር በላይ የሆኑና በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የታደሙባቸውን ዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ማስተናገድ የቻለችው ኢኮኖሚው የፈጠረላትን አቅም በመጠቀም ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

በአገሬ እያየሁት ያለው ለውጥ ለእኔም ሆነ ለወገኖቼ ኩራት ነው፡፡ ነገር ግን ለውጡ ዳር ደርሷል የሚል ድምዳሜ የለኝም፡፡ መንገዱን ግን ጀምሯል፡፡ ገና ብዙ መሰራት እንዳለበት ይገባኛል፡፡ እንደምሰማው መንግስታችንም በየአጋጣሚው የሚገልፀው ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡

የእስካሁኖቹ ስኬቶች የተገኙት ህዝብን ባሳተፈ መንገድ ተቀርፀው ተግባራዊ በተደረጉት የረጅም ፣ የመካከለኛና የአጭር ጊዜ ዕቅዶች አማካኝት መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ  ባለፉት ዓመታት በቅድሚያ «የዘላቂ ልማትና ድህነት ቅነሳ እቅድ» በኋላ ላይ ደግሞ፤ «ፈጣንና ዘላቂ ልማት ድህነትን ለማጥፋት» በሚል የተቀረፁት የመካከለኛ ጊዜ እቅዶች በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ በኢትዮጵያ ላለፉት አመታት የ11 በመቶ አማካይ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊመዘገብ እና ሀገራችን ያላት ገፅታ እና ተአማኒነት እያደገ ሊመጣ  የቻለው  በእነዚህ የልማት ውጥኖች አማካኝነት ነው፡፡

ይህንን የለውጥ ሂደት የበለጠ የሚያፋጥን መንገድ በጉዞ ላይ መሆኑን የአገራችንን ጉዳይ በቅርበት ለምንከታተል እንግዳ አይሆንም፡፡ ባለፈው ዓመት በይፋ የተጀመረውን የአምስት ዓመት እቅድ የመመልከት እድሉ ያጋጠመው የተቀመጡት የልማት ትኩረቶች የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ መዋቅር የበለጠ እንደሚያጠናክሩት የሚገነዘብ ይመስለኛል፡፡ 

በአገራችን አቆጣጠር እስከ 2007 የሚዘልቀው ይህ ብሄራዊ የልማት እቅድ ከአሁን በፊት ተግባራዊ የተደረጉት እቅዶች የፈጠሯቸውን ምቹ ሁኔታዎችን ይበልጥ አጠናክሮ በማስቀጠል አገሪቱን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ ይህ እቅድ በተገቢው መንገድ ተፈፅሞ እውን ከሆነ ለውጡ የትየለሌ ይሆናል የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ አለ፡፡

አንድ ነገር ግን አለ፡፡ ይህ የለውጥ ጎዳናችን በተለይ በከተሞች አካባቢ ዋጋ ንረትን የመሳሰሉ ፈተናዎች አጋጥመውታል፡፡ የዚህ ዓይነቱ ችግር ደግሞ የአገራችን ብቻ አለመሆኑን ማጤን ይገባል፡፡ ዓለም አቀፋዊ ገፅታ አለው፡፡ እንዲያውም በኢንዱስትሪ በልፅገዋል የሚባሉትን ጨምሮ በአብዛኛው የዓለም አገራት እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት ከእኛው በእጅጉ የከፋ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

በእኛ አገር በአሁኑ ወቅት የሚታየው የዋጋ ግሽበት የኢኮኖሚው እድገት ፍጥነት ያመጣው መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

የሆነው ሆኖ ግን የአገራችን መንግስት ይህንን ችግር ለመቅረፍ የተለያዩ የፖሊሲ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑ ለማናችንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በዚህ ረገድ አዎንታዊ ውጤቶች እየታዩ መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት በቅርቡ መግለፁን ሰምቻለሁ፡፡

በዋጋ ንረቱ ሳቢያ በተለይ በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለማገዝ ብሎ መንግስት በከፍተኛ ወጪ አንዳንድ መሰረታዊ ሸቀጦችን ወደአገር ቤት የማስገባት እርምጃ መውሰዱም ይታወቃል፡፡ ሆኖም ይህ ሸቀጥ በአግባቡ ተጠቃሚው ዘንድ እንዳይደርስ የሚያደርጉ ህገ ወጥ ተግባራት በአንዳንድ ግለሰቦች እየተፈፀመ መሆኑ መንግስት የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ በሚያደርገው ጥረት ላይ እንቅፋት እየሆነ መሆኑን እገነዘባለሁ፡፡

ይህንን ህገ ወጥ ተግባር በመከላከል ሸቀጦቹ ትክክለኛው ተጠቃሚ ዘንድ እንዲደርሱ የተለያዩ እርምጃዎችም እየተወሰዱ መሆናቸውንም እየሰማን ነው፡፡ ይህ ቁጥጥር ከተጠናከረ ችግሩን የመቅረፉ ተግባር የበለጠ ውጤታማ ይሆናል የሚል እምነት አለኝ፡፡

በሌላ በኩል የመጪው ዓመት የአገሪቱ ብሄራዊ በጀትም ችግሩን በመቅረፍ የግሽበት መጠኑን እጅግ ዝቅ ማድረግ በሚያስችል መልኩ ተዘጋጅቶ የሚተገበር ስለመሆኑም ከሳምንት በፊት የገንዘብ ሚኒስትሩ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማረጋገጣቸውን አድምጫለሁ፡፡

እናም ውድ ወገኖቼ! ከእውነት የራቀ ምንም ነገር የለም፡፡ ጥቂት ቆመው የቀሩ የአገራችን ፖለቲከኞችንና የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪነን የሚሉ አካላት አገራችንን አስመልክተው የሚያናፍሱትን መሰረት የሌለው ፕሮፓጋንዳ ቸል በማለት የለውጥ ጎዳናችን ይዘን እንግፋ፡፡
በአገራችን በራሱ  የሚናገርና አያሌችን የማረከ እውነት አለ፡፡ የተለያየ ፖለቲካዊ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች የአገራችንን ህዝቦች ለበለጠ ለውጥ እያነሳሳ የሚገኘውን ይህንን እውነት ለማጣጣል የሚነዙት ሟርት ጊዜ ያለፈበት ነው፡፡ ምክንያቱም ለውጡ ቀጥሏል፤ የአገራችን ጥቂት ተቃዋሞዎችና የውጭ ደጋፊዎቻቸው ሟርትም አልተቋረጠም፡፡

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ዜጎች ልብ ውስጥ እየጎመራ ያለው ተስፋ የማይጨበጥ ህልም አሊያም ባዶ ምኞች አይደለም፤ የሚታይና የሚዳሰስ ግዙፍ እውነት እንጂ፡፡ የዚህ እውነተኛ ለውጥ ታሪክ ሰሪዎችም ሆነ ባለቤቶች እኛ መሆናችንን ከቶም አንዘንጋ፤ የታሰበው ሁሉ ይሳካ ዘንድ የሁሉም ኢትዮጵያ ምኞች ነው፡፡ ለመጨበጥ የተቃረበው ይህ ምኞት እውን እንዲሆን ደግሞ መሰረቶቹ እኛ እንጂ ሌላ ማንም አይደለም፡፡


  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 170 guests