እንዱአለም አራጌና ሌሎች 23 ተከሳሾች የጥፋተኝነት ውሳኔ ተላለፈባቸው
አዲስ አበባ ሰኔ 21/2004/ዋኢማ/- የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትላንት በዋለው ችሎት አንዱአለም አራጌና ሌሎች 23 ተከሳሾችን በአሸባሪነት፣ ከፍተኛ የሀገር ክህደትና በስለላ ወንጀል የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላለፈ።
የፌዴራል አቃቤ ህግ በተከሳሾቹ ላይ ከፍተኛውን የእስራት ቅጣት እንዲተላለፍባቸውም ለፍርድ ቤቱ ጥያቄ አቅርቧል።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ እንደሻው አዳነ ለሁለት ሰአት ከሰላሳ ደቂቃ በፈጀ ንባብ የተከሳሾቹን መከላከያ በሙሉ ውድቅ በማድረግ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔውን አስተላልፏል።
የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዱአለም አራጌ፣ የፓርቲው አባል ናትናኤል መኮንን፣ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎች ስድስት ተከሳሾች ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት የተከታተሉ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 16 ተከሳሾች ጉዳያቸው በሌሉበት የታየ ነው።
የፌዴራል አቃቤ ህግ ተከሳሾቹ በሀገሪቱ አሸባሪ ተብለው ከተፈረጁት ግንቦት 7፣ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል በሽብር ወንጀል ከሷቸው ነበር።
ተከሳሾቹ ከኤርትራ መንግስት ጋር በመሆን በሀገራቸው ላይ የስለላና ከፍተኛ የሀገር መክዳት ወንጀል ፈፅመዋል ብሎ የከሰሳቸው ሲሆን ተከሳሾቹ ግን ይህን ክደው የተከራከሩ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ ሆነው አጊኝቷቸዋል።
በሌሉበት የጥፋተኛነት ውሳኔ ከተላለፈባቸው መካከል የግንቦት 7 መስራችና ከፍተኛ አመራሮች የሆኑት ዶክተር ብርሀኑ ነጋ፣ አንዳርጋቸው ፅጌና መስፍን አማን ይገኙበታል። የግንቦት 7 ልሳን ነው በተባለው የኢሳት ቴሌቪዝን የቦርድ አባል የሆኑት አበበ ገላውና አበበ በለው ሌሎች በሌሉበት ጥፋተኛ የተባሉ ናቸው።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አዳራሽ ከወትሮው በተለየ ሁኔታ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ጋዜጠኞች፣ በተከሳሽ ቤተሰቦች፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ዶናልድ ቡዝን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ዲፕሎማቶች፣ የፓርላማ አባልና የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሴፉን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሰዎች ችሎቱን ተከታትለውታል።
| < Prev | Next > |
|---|


