ለትምህርት ቤቶች የተለቀቀው የድጎማ በጀት ለትምህርት ጥራት መምጣት አስተዋጽኦዉ የጎላ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ተናገሩ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20 /2004 (ዋኢማ) - ከአለም ባንክና ከአለም አቀፍ የልማት አጋሮች ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ለሁሉም ትመህርት ቤቶች የተለቀቀው የድጎማ በጀት ለትምህርት ጥራት መምጣት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ተናገሩ።

የትምህርት ቤት ርዕሳነ መምህራንም የድጎማ በጀቱ መለቀቁ በርካታ የትምሀርት ግብአቶችን እንድናሟላ ረድቶናል ብለዋል።

ሰሞኑን ይፋ የተደረገ የአለም ባንክ ሪፖርት እንዳረጋገጠውም 98 በመቶ የኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የድጎማዉ ተጠቃሚ ሲሆኑ 95 በመቶዎቹ ደግሞ የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ መጠቀማቸውን አረጋግጫለሁ ነዉ ያለዉ።

የላብራቶሪ ክፍሉ እንዲህ እንደዛሬዉ በማስተማሪያ ኬሚካሎችና ቁሳቁሶች የተሟላ አልነበረም።

የተማሪዎች አጋዥ መጻህፍትም በሼልፍ በአይነት በአይነታቸዉ ተደርድረዉ ማየትና አማርጦ ማንበብ የማይቻልበት ጊዜ ነበር።

የቤተ መጻህፍት ወንበሮችና ጠረጴዛዎችም እዚህና እዛ ጣል ጣል ተደርገዉ ሲታዩ ለማጥናት ብለዉ ወደ ዉስጥ ዘልቀዉ የሚገቡ ተማሪዎችን ያሳቅቁም ነበር።

ጥቂት መጽሃፍትና በቂ ያልሆኑ ወንበሮችም ተማሪዎቹን የማንበብ ፍላጎት እንዳይኖራቸዉ ማድረጉ ሌላዉ ፈታኝ ሁኔታ ነበር።

ይህ ሁሉ ለብዙ የሀገራችን ትምህርት ቤቶች  የትናንት ትዝታ ሆኗል።
ዛሬ ቀኑ ሌላ ነዉ።

ይህን ሁሉ በትዉስታ የሚያስቀር መልካም ነገር ምን ተገኘ አልኳቸዉ የትምህርት ቤቱን ርዕሰ መምህር አቶ መላኩ።

መንግስት የቀረጻቸዉ የአጠቃላይ ትምህርት ማረጋገጫ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ ለማድረግ የተለቀቀ የድጎማ በጀት መኖሩን ነገሩኝ።

ይህ የድጎማ በጀት የተለቀቀው በአለም ባንክና በሌሎች አለም አቀፍ የልማት አጋሮች መሆኑን ለማረጋገጥ ችያለሁ።

በተለይ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በሀገር አቀፍ ከተለቀቀዉ በጀት ነዉ ትምህርት ቤታችን ገሊላ ተጠቃሚ የሆነዉም ብለዋል።

በጀቱ ለመንግስት፤ ለህዝብና ለአማራጭ መሰረታዊ ትመህርት ቤቶች ይለቀቃል።
ለትምህርት ቤቶች ለማድረስም ዋና መመዘኛዉ የተማሪዎች ቁጥር ነዉ።

ከ2002 ዓ፡ም ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ያለዉ ይህ የድጎማ በጀት ብዙ ሺ የሀገራችንን ትምህርት ቤቶች ያሉባቸዉን የቁሳቁስና ሌሎች ችግሮችን እንዲፈቱ እንዳስቻላቸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የጥናት እቅድና በጀት አስተባባሪ አቶ ታከለ ዴሳ ተናግረዋል።

ለመጀመሪያ ጊዜ ተግባራዊ ሲደረግ ለአንድ ተማሪ በሴሚስተር 15 ብር ይመደብ ነበር። ዛሬ ላይ የብር መጠኑ ወደ 60 ብር እንዲያድግ ተደርጓልም ይላሉ።
በዚህ ቀምር መሰረት አንድ ሺ ተማሪዎቸን የሚያስተምር አንድ የ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአንድ መንፈቅ አመት 60 ሺ ብር ያገኛል ማለት ነዉ። ይህ ነዉ እንግዲህ ለትምህርት ቤቶች የዉስጥ ችግርን ለመቅረፍ ጥሩ መፍትሄ ሆኖ ቀረበ የሚባለዉ።

ከጅኩፕ በፊት የነበሩብንን የትምህርት ግብዓት እጥረቶችን በመንግስት መደበኛ በጀት ብቻ ማሟላት ባለመቻላችን በትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተፅኖው ከባድ እንደነበር የሚያስታውሱት የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምሀር አሁን ብዙ ነገሮች ተቀይረዋል ይላሉ። በትምህርት ጥራት ላይም እየታዩ ያሉት ለውጦች በርካታ ናቸው።

እነዚህ ሁሉ ለውጦች መምጣት የቻሉት ግን ለትምህርቱ አጋዥ የሆኑ ቁሳቁሶች እየተሟሉ በመምጣታቸው እንደሆነም ይናገራሉ።
ርዕሰ መምህሩ አክለውም በቅርብ አመታት እናሟላቸዋለንና እናሳካቸዋለን  ብለን የማናስባቸው ሌሎች ቁሳቁሶች የተሟሉትም በጂኩፕ ገንዘብ ነዉ ብለዋል።

በሌላ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር የሆኑት አቶ ያዕቆብ አዲስ እንደሚሉት ድጎማው የሚለቀቀው ግልፅ በሆነና ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ ነው።    

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የጥናት እቅድና በጀት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ታከለ ዴሳ የሚገልፁትም ርዕሳነ መምህራኑ በድጎማ በጀቱ አገኘን የሚሉትን ጥቅም ነው።

የትምህርት ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንንም ጂኩፕ በትምህርት ቤቶቻችን የተሻለ ለውጥ እንዲመጣ አድርጓል ይላሉ።
ሰሞኑን የአለም ባንክ ያወጣው ሪፖርት ያረጋገጠውም ይሄንኑ የኢትዮጵያን መልካም አፈፃፀም ነዉ።

ባንኩ እንደሚለው ኢትዮጵያ የተመደበላትን በጀት በአግባቡ ተጠቅማለች። 98 በመቶ የሚሆኑት የሀገሪቱ ትምህርት ቤቶች የአመታዊ የድጎማ በጀቱ ተጠቃሚዎች እንደነበሩ ማረጋገጡን በሪፖርቱ ጠቁሟል።
ድጎማው ከተፈቀደላቸው ትምህርት ቤቶች መካከልም 95 በመቶ የሚሆኑት የተመደበላቸውን በጀት በአግባቡ ተጠቅመዋልም ይላል።

95 በመቶዎቹ ደግሞ ገንዘቡን የተጠቀሙት በትምህርት ቤት መሻሻል ላይ እንደሆነ አትቷል።

የአለም ባንክ በማጠቃለያው መንግስት ለትምህርቱ ዘርፍ የሰጠውን ትኩረት አድንቆ በማሳያነትም ከአጠቃላይ የሀገሪቱ በጀት ከ25 በመቶ በላይ ለትምህርት እንዲውል ማድረጉንም ያወሳል፤ ዘገባው የፋና በሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ነው።



  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 239 guests