ከህዝበ ሙስሊሙ ምን ይጠበቃል?

  • PDF

(ክፍል ሁለት)
ሲኢድ መሐመድ

በክፍል አንድ ጽሁፌ ከህዝበ ሙስሊሙ የሚጠበቁ በርካታ ጉዳዮችን አንስቸ ነበር፡፡ በተለይም በአገራችን ያለው አክራሪነት ካለው ሃይማኖታዊ ተልእኮ ይልቅ ፖለቲካዊ ተልእኮውን አጉልተው የሚያሳዩ በርካታ አብነቶች ተጠቅሰዋል፡፡ የግንኙነት መስመሩም ኢትዮጰያን ማፈራረስ ከሚፈልጉ አሸባሪ ወገኖች ጋር እንደሆነ ለማየት ተሞክሯል፡፡ በዚህ ሁለተኛና የመጨረሻ ክፍል ደግሞ ህዝበ ሙስሊሙ ከአላህ አስተምሀሮ እንዳይወጣ፣ መንገዱን እንዳይስትና አሁን በአገራችን በእስልምና ሃይማኖት አማኞች መካከል እየተፈጠ ያለው ልዩነት ከአላህ መንገድ የወጣ መሆኑንና ከዚህ አንጻር ህዝበ ሙስሊሙ ምን ማድረግ እንዳለበት ለማየት ተሞክሯል፡፡

“የአህባሽ እምነትና አስተምህሮት ይቁምልን፤ እኛ የምንከተለው እምነት ብቻ ይሰበክ፤ ይነገር፤ ከኛ እምነት ውጪ ሌላው ከምድር ይወገድ“ የሚል አጀንዳ ያነገቡት እነዚህ ጽንፈኞች ህዝብ ውስጥ ሰርገው ገብተው ትርምስ በመፍጠር ላይ ናቸው፡፡ በርካታ ሙስሊሞችን፣  የመስጊድ ኢማሞችና እና ሙዐዚኖችን በተለያዩ አካባቢዎች ደብድበዋል አንገላተዋል፡፡ እነዚህ ጽንፈኞች በዋናነት በተለያዩ የውጭ አክራሪ ድርጅቶች እንደሚደገፉም ተረጋግጧል፡፡ በመላ አገሪቱ ያሉ ኢስላማዊ ድርጅቶች፣ መስጊዶች እና ጀመዓዎችን የግድ የእነሱ እምነት ተከታይ ካልሆኑ በስተቀር የቻሉትን እርምጃ በመውሰድ ያልቻሉትን ደግሞ በማስፈራራትና በማሸማቀቅ ለማሳደድ እየሞከሩ ነው፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ መጀመሪያ የአክራሪ ቡድኑን ማነነት ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል፡፡ ከዚያም በስሙና በተቀደሰው ሃይማኖቱ ስም መነገዳቸውን እንዲያቆሙ ከመንግስትና ከሌሎች ሰላም ወዳድ ወገኖች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ መስራት አለበት፡፡ የእስልምና ሃይማኖት ቅርሶችንና የእምነት ቦታዎችን በማጥፋት የእስልምናን ታሪክ ለመሰረዝ ጽንፈኞች ወደኋላ አይሉም፡፡ ይህ ደግሞ  የሚኖረው አደጋ ቀላል አይሆንም፡፡

ሕገ ወጥነት መገታት ስላለበት በዚህ ጉዳይ ላይ ዳር ቆሞ የሚመለከት አንድም የሙስሊሙ ሕብረተሰብ አባል ሊኖር አይገባም፤ የመንግስት ሃላፊዎችም እንደዚያው፤ ሌላው ሰላም ወዳድ ሕብረተሰብም የዚያን ያህል መስራት ይጠበቅበታል፡፡

እስካሁን ከቀረበው አጠቃላይ ሃሳብ በመነሳትም ከህዝበ ሙስሊሙ ምን ይጠበቃል? የሚለውን ጥያቄ ምላሽ ለማጠቃለል በሚከተሉት ዓበይት ነገሮች ላይ አጽንኦት መስጠት  የግድ ይላል፡፡

በእውነት መመስከር ለምድር እንዳይደል ሁላችንም እናውቃለን፡፡ ምስክርነታችንን ለአላህ ስንልም እናደርጋለን፡፡ አላህ ውሸትንና ቅጥፈትን፤ ሁከትንና ብጥብጥን አይፈልግም፡፡ ነገ ወደ እሱ መሄዳችን አይቀሬ በመሆኑ ያገኘነውን እንዳላገኘን ብንናገር በመጨረሻው ስዓት በሱ ፊት ከተጠያቂነት አንድንም፡፡ እናፍናችኋለን የሚሉ ጽንፈኞችን በመፍራትስ ህዝበ ሙስሊሙ ስለምን ይሸማቀቃል?

የእስልምና ሃይማኖት አባቶቻችን እንዳስተማሩንና በቁርኣኑም እንደሰፈረው  “እነርሱን አትፍሯቸው፣ እኔን ብቻ ፍሩ፤” ይላል፡፡  አሁን ሃይማኖታዊ ለምድ ለብሰው የመጡት ጽንፈኞች ከአላህ ዘንድ አይደሉምና ልንፈራቸው አይገባም፡፡ አላህ ሰውን ግደል የሚል አስተምህሮ የለውም፤ እኔ ብቻ ብጹእ ነኝ እንዲል ለሰው የሰጠው መንፈሳዊ ትምህርትና ሥልጣንም የለም፤ ሁሉም ህዝበ ሙስሊም የሚያውቀውን መድገም ይሆንብኛል እንጂ  “ከአላህ በስተቀር ፍጹም የለም”፡፡

ዘመኑ የወለዳቸው አክራሪዎች ግን "ቅዱሳንና ብጹአን እኛ ብቻ ነን" እኛን ተከተሉ በማለት የራሳቸውን ፍላጎትና በተለይም ከውጭ የተሰጣቸውን ተልዕኮ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ በኃይል ለመጫን እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ከአላህ ዘንድ አይደሉምና ህዝበ ሙስሊሙ ሊታገላቸው ይገባል፡፡ እነዚህ ትክክለኛ የሃይማኖት ተልእኮ የላቸውምና ሊወገዙ ይገባል፡፡ ቦታና ጊዜ አግኝተው ሃይማኖታችንን ሊፈታተኑትና አንድነታችንን ሊበትኑት አይገባም፡፡

በየጊዜው ሀሳዊ መሲሓን በተነሱ ቁጥር አይደናገርም ሊደናገርም አይገባም፡፡  ሐሰተኞች የሚበዙበት ወቅት ይመጣል እንደተባለው እነዚህም ወዳጆቻውን ሁሉ ሳይቀር ያስፈራራሉ፤ እኛ ያልነውን ተከተሉም ይላሉ፤ ከዚያም አልፈው ወዳጆቻቸውንም ሳይቀር ይገድላሉ፤ ታሪክና እምነትን ያጠፋሉ ሆኖም ግን "እነሱን አትፍሯቸው፤ ከአላህ አይደሉምና ይላል፡፡” (ቁርኣን ዓሊ-ኢምራ 3፡175) ፡፡

ህዝበ ሙስሊሙ ሃይማኖቱን ለማጥፋትና አንድነቱን ለመሸርሸር አቅደው በመንቀሳቀስ ላይ ያሉትን ጽንፈኞች ሊዋጋቸው፣ ለሕግ ሊያቀርባቸውና ጉያው ውስጥ እንዳይደበቁ እርቃናቸውን ሊያወጣቸው ይገባል፡፡

በአገራችን ለዘመናት የዘለቀው የእስልምና ሃይማኖት ከሌሎች የአገሪቱ ሃይማኖቶች ጋር ተጣጥሞ የኖረ ነው፡፡ አገሪቱ የሁሉም ሃይማኖት አማኞች በጋራ ተሰስበውና ተደጋግፈው የሚኖሩባት አገር ነች፡፡  አሁን እየመጣ ያለው  የአክራሪዎች ሕግ ግን ከሌሎች የሃይማኖት አማኞች ጋር በሰላም መኖር ይቅርና ህዝበ ሙስሊሙን እርስ  በርስ ግጭትና ሁከት ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡

ይህ ቡድን  ባገኘው መንገድ ሁሉ  የሙስሊሙን ሕብረተሰብ  ለማዋጋት፣ እርስ በርስ ለማጋጨት፣ ከሚከተለው እምነት ወደ ክህደት ለመመለስ የሚያስገድድ ነው፡፡ ይህ አካሄድ ከአላህ አስተምህሮና ትእዛዝ ጋር የተጋጨ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች እምነታቸውን የከዱና ለምድራዊ ስልጣን እና ለስጋቸው ያደሩ  ናቸው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ ከሚከተለው እምነት ያፈነገጠ እምነት ለመተግበርም የተነሱ ናቸው፡፡ በእምነት ስም ሌላ አጀንዳ አንግበው የሚታገሉ የፖለቲካ ቅጥረኞች ናቸው፡፡

እርግጥ ነው የአላህ አስተምህሮ “ከውስጣችሁ ይህችን ዓለም የሚሹ አሉ፤ የመጭውን ዓለም ስኬት የሚሹም አሉ” ይላል፡፡ ይህችን ዓለም የሚመኙ በዚች ዓለም ላይ መንግስት ሆነው መሬትን ማስተዳደር በመሬት መንገስ የሚሹ ከአላህ ፈቃድ የወጡ ጽንፈኞች አሁን ተከስተዋል፡፡ እኛ ሙስሊሞች እነዚህን የአላህን መንገድ ተጻረው ወንድም ወንዱሙን እንዲገድል እየሰበኩና   በሃይማኖት አማኞች ዘንድ መቻቻልና አብሮነት እንዲጠፋ እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

ስለሆነም ጀነትና አኪራን የሚፈልግ ሁሉ እስልምናን ለማጥፋት  ከተነሱ  ከሃድያንና ተባባሪዎቻቸው ጽንፈኞች  ሴራ ራሱንና መላውን ሙስሊም መከላከል ይኖርበታል፡፡  ይህንን ጸረ-ኢስላም ዘመቻ እያካሄደ ያለው አክራሪ ቡድን  የከሰሩ ፖለቲከኞችና  ኪራይ ሰብሳቢ ሙስሊሞች የተሰገሰጉበት ነው፡፡

መንግስት የሁሉም ዜጋ መብት በእኩል ደረጃ የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡  ይሁን እንጂ ይሄኛውን ሃይማኖት ተከተሉ ይህንን አትከተሉ የሚልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ይህንን ለማድረግ የአገሪቱ ሕገመንግስት አይፈቅድለትም፡፡ በመሆኑም የአልአህብሽ አስተምሀሮ ይቁምልን የሚለውን ጥያቄ ማስተናገድ አልቻለም፡፡

የአልሃብሽ አስተምህሮም ሆነ የሌሎች እምነቶች አስተምህሮዎች ሃይማኖታዊ  ተልእኳቸውን ሳይስቱ ያለምንም ችግርና ስጋት ሊካሄዱ ሕጉ ይፈቅዳል፡፡ አሁን እያከራከረን ያለው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ መስጠት ወይም ሃይማኖታዊ  ተልእኮ ለመወጣት ነጻነት ማጣት ወይም የእምነት ስፍራ ማጣት አይደለም፡፡

እንደዚህ  ዓይነቱ  ጥያቄ የነበረው ቅድመ ሁለት አስርት ዓመታት ነበር፡፡ ያኔ የእስልምና ሃይማኖት አማኞች በግላጭ አደባባይ የማይወጡበትና በነበሯቸው ጥቂት የእምነት ስፍራዎች ለመሰባሰብና ሃይማኖታዊ ተልእኳቸውን ለመፈጸምም የሚሸማቀቁበት ወቅት ነበር፡፡ ተሰባሰባችሁ በሚል  የሚታሰሩበት፣ የሚገረፉበትና የሚገደሉበት ወቅት፡፡ ሁሉም ህዝበ ሙስሊም የሚያውቀው ነገር መድገም አይሁንብኝና  አሁን ያ ሁሉ ነገር የለም፡፡  ህዝበ ሙስሊሙ በአደባባይ የሃይማኖት በዓላቱን በደመቀ ሁኔታ ያከብራል፡፡ በአገሪቱ ከ60-70 ሺ የሚሆኑ የእምነት ስፍራዎችን መገንባት ችሏል፡፡ እምነቱንና ከእምነቱ ጋር በተያያዘ የሚያደርጋቸው ማንኛውም እንቅስቃሴዎች በነጻነት እየከወነ ይገኛል፡፡

የሃይማኖት ነጻነት በተረጋገጠበት አገር ግን የሌላን ሃይማኖትና አስተምህሮ አፍናለሁ የሚል ቡድን ሕጋዊ መሰረት ሊኖረው አይገባም፡፡ አሁን በአገራችን ያለው አክራሪነት የእስልምና ሃይማኖትን  የመቦርበር ፤ ስር መሰረቱን የመበረዝ ተግባር ነው፡፡  ስለሆነም ሁሉም  የሙስሊሙ ሕብረተሰብ ለዲናው ሲል በየአካባቢ እየተደራጁ ኢስላማዊ እንቅስቃሴዎቻችንን ለማወክና ሰላማችንን ለማደፍረስ እየተራወጡ ያሉትን ጽንፈኞች በጋራ መዋጋትና ወደ ሕግ ማቅረብ ይጠበቅበታል፡፡ 

ለዚህም በየመስጊዶች፣ መድረሳዎች፣ ጀመዓዎች፣ በየመስሪያቤቶች፣  በየሰፈር፣ በየቤተሰብና  በእድሮች በሚኖረን ግንኙነት ሁሉ  አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን  የአገርን ሰላም ለማደፍረስ የእስልምና ሃይማኖትን ማንነት ለማጥፋትና ሙስሊሙን እርስ በርስ ለማፋጀት ዓልሞ የተነሳ በመሆኑ ዉይይት እያደረገ  መፍትሄ  መፈለግ ይጠበቅበታል፡፡ የሃይማኖታችን ማንነት መገለጫ ስፍራዎችንና ቅርሶችን ለማጥፋት አልሞ ከተነሳው  አክራሪ ቡድን ራሳችንንና ሃይማኖታችንን  መጠበቅ የግድ ይላል፡፡

ይህ የጽንፈኞች ቡድን የተለያዩ  ሚዲያዎችን በመጠቀም ሕብረተሰቡ ዘንድ ብዥታ ለመፍጠር እየጣረ ይገኛል፡፡ ሰለፊያ የሚባለው ጋዜጣም በዋናነት የህዝበ ሙስሊሙን አንድነት ለማናጋት ዘገባውን ቀጥሏል፡፡  ሌሎች ጽንፈኛ ጋዜጦችም  ችግሩን ለማባባስና የአገሪቱን ሰላም ለማወክ ያስችል ይሆናል በሚል  ማራገቡን ተያይዘውታል፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ የእነዚህ ጽንፈኛ ጋዜጦች ሰለባ ከመሆን ራሱን መጠበቅና የዚሁ ሰለባ ሊሆኑ የሚችሉትን ሁሉ ማስተማር ይጠበቅበታል፡፡

የሚዲያው ቅንብር በስደት በሚገኘው የግንቦት 7 አሸባሪ ቡድን ሃይሎችንና ሌሎች ተቃዋሚዎችም የሚሳተፉበት በመሆኑ እነዚህ ጽንፈኞች እያደረጉ ያሉትን ጸረ ህዝብ ተግባራትን ማጋለጥ፣ በየመስጊዱና በእምነት ስፍራዎች እየተገኙ ህዝበ ሙስሊሙ ከፈጣሪው ጋር ለመገናኘት የሚመጣበት ወቅት እየጠበቁ ብጥብጥ መፍጠርና ሌሎች እኩይ ተግባራትን የሚፈጽሙ የተደበቀ ዓላማ ያላቸው መሆናቸውን ለልጆቻችንና ለምንቀርበውና ለምናውቀው ሙስሊም ማሳመን ከኛ ይጠበቃል፡፡ ይህን ሁሉ የምናደርገው ለኢህአዴግ ብለን አይደለም፡፡ ለመንግስትም አይደለም፤በአላህ ፊት ሃቅን ለመከተል፤ ህዝባችንን ከአደጋ ለመጠበቅና ሃይማኖታችንን ለመታደግ እንጅ፡፡

አላህ የሃቅ፣ የእውነት፤የፍቅርና የሰላም ተምሳሌትና ቋት ነው፡፡ በሃሰት እንዳንመሰክርም ያስተምረናል፡፡ እኛ ዛሬ ላይ ቆመን በኢትዮጵያ የእስልምና አማኞች መብታቸው ተረግጧል የሃይማኖት ነጻነታቸውን አጥተዋል ብንል ይፈርድብናል፤በጥበቡ የሃይማኖት ነጻነት እንድናገኝ አድርጎናልና፡፡  አሁን የክህደት ቃል እንድንመሰክር የሃይማኖት ነጻነት በአገራችን የለም እንድንልና ከእነሱ ጋር ተባብረን እንድናምጽ የሚገፋፉን ቡድኖች ከአላህ ስላይደሉ  ሃይማኖዊ  ተልእኮ ሳይኖራቸው በተቀደሰው ሃይማኖታችንና በህዝበ ሙስሊሙ ስም የሚነግዱ በመሆናቸው በጋራ ልንዋጋቸው ይገባል፡፡

በየዳዕዋ ጀመዓዎቻችን፣ የዳዕዋ ጀመዓዎች ያለፍራቻ በግልጽ የእነዚህን አክራሪዎች ማንነት ህዝቡ እንዲያውቅ ማስተማር፤ የሙስሊሙን አንድነት ለማፍረስ የሚታገሉትን የኢስላም ጠላቶች በተቻለው መንገድ ሁሉ ሰዉ እንዲያውቃቸውና ከሚዘረጉት መረብ እንድንጠበቅ ማስቻል ይኖርብናል፡፡

ጽንፈኞቹን ለመዋጋት በሚደረገው ጥረት መላውን የሙስሊም ሕብረተሰብን ማሳተፍ፡፡  በጽንፈኞቹ የሚሰራጩ የፕሮፖጋንዳና የቅስቀሳ ተግባራት ባዶነትን ማስተማር፡፡ በየዋህነትና በቅንነት ከአላህ የሆኑ መስሏቸው የተሳሳቱን ወገኖች በአስተምህሮ መመለስ ከኛ ይጠበቃል፡፡

በህዝበ ሙስሊሙ መካከል እሰካሁን የተፈጠረው  ልዩነት እንዳይሰፋ መጣር፣ በከተማም ሆነ በገጠር ህዝበ ሙስሊሙን ማረጋጋትና የጽንፈኞች ውዥንብር ሰለባ እንዳይሆን ማድረግ፤  ዑለሞች የመዝሀብ ልዩነት ሳይኖራቸው አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን በመዋጋት  ላይ በጋራ እንዲሰሩ አብረው እንዲያወግዙ-ፈትዋ እንዲሰጡ ማድረግ ሀይማኖታችንንና ራሳችንን ከአክራሪዎች አደጋ ለመጠበቅ ያግዛል፡፡

በተለያዩ ተቋማት፣ በድርጅቶችና ሌሎች የህዝብ መገናኛ ስፍራዎች አክራሪነት ምን ያህል ጎጂ እንደሆነና አሁን በአገራችን ህዝበ ሙስሊሙን ለመለያየትና ለማፋጀት የተወጠነው ነገር ለህዝበ ሙስሊሙ ፋይዳ የሌለው ከራሱ አልፎ ሌላውን የአገሩን ህዝብ የሚጎዳና  ሃይማኖታዊ ተልእኮውን በነጻ እንዳያራምድ የሚከለክል በመሆኑ ይህንኑ ያገናዘበ ትብብር ማድረግና ጸረ ሰላም ኃይሎችን ቦታ ማሳጣት ይገባል፡፡

የጀማዓችንን አንድነት ለማናጋትና  የህዝበ ሙስሊሙን ማንነት  ለማጥፋት  የሚንቀሳቀሱት ጽንፈኞችንና የእነሱን አስተምህሮ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚከተሉትን መለየትና ትክክለኛውን መንገድ እንዲይዙ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

በማንኛውም ሚዲያ የሚተላለፉ ዘገባዎችና ህዝበ ሙስሊሙን የሚመለከቱ ነገሮችን በጥልቀት መመርመር እንጂ አንዳንድ ጽንፈኛ ሚዲያዎች በሚያስተጋቡት የበሬ ወለደ ወሬ ውዥንብር ውስጥ መግባት አይኖርብንም፡፡ በመሆኑም  በዩኒቨርሲቲያች፣ ኮሌጃችና ትምህርት ቤቶች፣ በመስጊዶችና ሌሎች ስፍራዎች የምንገኝ የሙስሊም ሕብረተሰብ አባላት ህዝባችንን ከጽንፈኞች አደጋ ለመጠበቅና አክራሪዎቹ የወጠኑትን   ሴራ ለማክሸፍ እጅና ጓንት ሆነን መስራት ይጠበቅብናል፡፡ 









  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 278 guests