አሚሶም የኤልማን ወደብንና የኢሳሌ አየር ማረፊያን ከአልሸባብ አሸባሪዎች አስለቀቀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 18/2004 (ዋኢማ) -  የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ(አሚሶም)በማዕከላዊ ሸበሌ ግዛት የኤልማን ወደብንና የኢሳሌ አየር ማረፊያን ከአልሸባብ አሸባሪዎች አስለቀቀ።
የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቀው ተልዕኮው የአገሪቱን የባህርና የአየር መገናኛ ሥፍራዎች የተቆጣጠረው በሶማሊያ ሰላም ለማስፈን በጀመረው እንቅስቃሴ ነው።
ተልዕኮው የሶማሊያ ብሄራዊ ሠራዊትን በመደገፍ ከአልቃይዳ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ያለውን አሸባሪ ኃይል ለመቆጣጠር በወሰደው እርምጃም ከሞቃዲሾ 37ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትን ከተሞች በቁጥጥር ሥር ለማዋል በቅቷል።የጦር መሣሪያዎችንም ማርኳል።
አልሸባብ ከተሞቹን ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችንና ከውጭ የሚገቡ ተዋጊዎችን ወደ ሶማሊያ አስርጎ ለማስገባት ይጠቀምባቸው እንደነበርም መግለጫው አመልክቷል።
በተጨማሪም በደቡብ ሶማሊያ ሰብዓዊ ቀውስ ለደረሰባቸው ዜጎች ዕርዳታ እንዳይገባ የአየር ማረፊያውን ላለፉት ስድስት ዓመታት ያህል ዘግቶት መቆየቱንም ኮሚሽኑ ገልጿል።
የአሚሶም አዛዥ ሌተና ጄኔራል አንድሪው ጉቲ ''በሠራዊታችን በተደረገው የተሳካ ዘመቻ ወደ ሞቃዲሾ የሚያስገባውን ስትራቴጂካዊ ሥፍራ መቆጣጠር ችለናል።የሠራዊቱ የሰው ኃይል ወደ 17ሺህ331 ካደገ ወዲህ የአሚሶም ኃይሎች በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚያስችለን አቅም ጎልብቷል'' ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እንደ ኢዜአ ዘገባ አልሸባብ ከአፍጎዬ አካባቢ ሸሽቶ ተጠልሎባቸው የነበሩት ከተሞች መያዝ ወደ ባህር ዳርቻዎች የሚያደርገውን ሽሽት እንዲገፋበት ማድረጉንም መግለጫውን ጠቅሶ የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 420 guests