የስደተኞች ቀን መከበሩ የስደተኝነትን አስከፊ ህይወት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት እንደሚረዳ ተጠቆመ

  • PDF

አዲስ አበባ ሰኔ 14/2004/ዋኢማ/ - የስደተኞች ቀን በየዓመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበሩ የስደተኝነትን ህይወት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳየት እንደሚረዳ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ አስተዳደር አስታወቀ። “አንድም ቢሆን ብዙ ነው” በሚል መሪ ቃል የዓለም የስደተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሯል።

አስተዳደሩ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል በላከው መግለጫ፤ የስደተኞችን ህይወት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳየት የስደተኞች የኑሮ ሁኔታን ለማሻሻልና የለጋሽ አገራትን ትኩረት ለማግኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖረዋል።

በአሁኑ ወቅት በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞችና ተፈናቃዮች በዓለም ዙሪያ እንደሚገኙ የጠቆመው መግለጫው፤ እ.ኤ.አ በ2011 ብቻ ተጨማሪ 800 ሺ አዲስ ስደተኞች አገር አቋርጠው ተሰደዋል። ይህም እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ ከፍተኛ ቁጥር ሆኖ ተመዝግቧል።

ኢትዮጵያም ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነርና ከዓለም የምግብ ድርጅት ጋር በመተባበር ለስደተኞች ከለላ በመስጠት ፈርጀ ብዙ ስራዎችን እያከናወነች መሆኗን መግለጫው የገለፀ ሲሆን፤ በ2011 ብቻ 137ሺ ስደተኞችን ከሱማሊያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳንና ሱዳን ተቀብላለች።

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከ345 ሺ በላይ ስደተኞች በ18 የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ መግለጫው ገልጿል።

ስደተኞችን ተቀብሎ ማስተናገዱ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ድርሻው የጎላ  መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል።

“አንድም ቢሆን ብዙ ነው” በሚል መሪ ቃል የዓለም የስደተኞች ቀን ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከብሮ የሚውል ሲሆን፤ ቀኑ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለ12ኛ ጊዜ በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ የስደተኛ ጣቢያዎችና በአዲስ አበባ ተከብሮ ውሏል።

በተለይም በትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ውስጥ በሚገኘው በማይዓይኒ የኤርትራ ስደተኞች መጠለያ ጣቢያ በዓሉ በደመቀ ሁኔታ የተከበረ ሲሆን፤ በበዓሉ ላይ የለጋሽ አገራት አምባሳደሮች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ኃላፊዎችና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅት ተወካዮች ተገኝተዋል።

የዓለም የስደተኞች ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ሰኔ 13 ቀን እንዲከበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እ.ኤ.አ በ2000 በየዓመቱ “የዓለም የስደተኞች ቀን” ተብሎ እንዲከበር ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት መከበር መጀመሩ ይታወሳል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 224 guests