ቻይና የመጀመሪያዋን ሴት ጠፈረተኛ ወደ ኅዋ ላከች

  • PDF

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 11/2004 (ዋኢማ) -ቻይና የመጀመሪያዋን ሴት ጠፈረተኛዋን ትናንት ወደ ኅዋ ላከች።

ኢዜአ የቻይና ዜና አገልግሎትን ጠቅሶ እንደዘገበው አገሪቱ ሊዩ ያንግ የተባለች የ33 ዓመት የአየር ኃይል መኮንን ከሁለት ወንዶች ጋር ወደ ጠፈር ልካለች።

ጠፈረተኛዋ ''ሼንዡ ዘጠኝ''በተባለችው መንኩራኩር በሰሜናዊ ምዕራብ ቻይና ከምትገኘው የጂዑኪያን የኅዋ ማምጠቂያ ማዕከል መጥቃለች።

ቻይና ወደ ኅዋ ሴት ጠፈረተኛ በመላክም በዓለም ሦስተኛ አገር ሆናለች።

መንኩራኩሯም ለ13 ቀናት ተልዕኮዋን እንደምታከናውንም ዘገባው ያስረዳል።

በሄናን ክልል የተወለደችው ሊዩ የአየር ኃይል ሻለቃና የኮሙኒስት ፓርቲው አባል ስትሆን፣ምድርን ከኅዋ ላይ ሆና ለማየት ፍላጎት እንዳላት ስትገልጽ ቆይታለች።

''የቻይናን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን ሴቶች ወክዬ ወደ ጠፈር በመጓዜ ክብር ይሰማኛል''ስትል ባለፈው ዓርብ ለጋዜጠኞች ተናግራለች።

ሻለቃ ሊዩ በኅዋ ቆይታዋ የሕክምና ሙከራዎችንና ሌሎች የኅዋ ምርምሮችን ከጓደኞቿ ጋር እንደምታደርግም ዘገባው አመልክቷል። ለጉዞው የሚያስፈልጋትን የሁለት ዓመታት ሥልጠና ተከታትላለች።

ባለቤቷ ለጉዞዋ መቃናት ላደረገላት ሁለንተናዊ ድጋፍ ምስጋናዋንም አቅርባለች።

የመንኩራኩሯ አዛዥ ጂንግ ሐይፔንግ በሰጡት አስተያየት ሊዩ ሥልጠናውን ዘግይታ ብትጀምርም፤አሁን ከበረራ ጓደኞቿ እኩል የሚያደርጋትን ብቃት መጎናጸፏን ገልጸዋል።ይህም ከግምታቸው በላይ እንደሆነም አስታውቀዋል።

ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ጠፈርተኛ ጠንካራ ሠራተኝነቷ፣አንባቢነቷ፣ምግብ አብሳይነቷና መልካም ባህርይዋ በሥራዋና በማዕከሉ ሠራተኞች ዘንድ ተወዳጅ እንዳደረጋት ዘገባው ይገልጻል።

የቻይናው ፕሬዚዳንት ሁ ጂንታኦ በጉብኝት ላይ ከነበሩበት ከኮፐንሐገን፣ዴንማርክ ባስተላለፉት መልዕክት አገሪቱን በኅዋ ምርምር አንድ እርምጃ በሚያራምደው ፕሮግራም ባስገኘው ውጤት መደሰታቸውን ገልጸዋል።

የአውስትራሊያው የኅዋ ገምጋሚ ሞሪስ ጆንስ በዓለም በሚካሄዱ የኅዋ ፕሮግራሞች በርካታ ሴቶች ማየት እንደሚፈልጉና ይህም የኅዋ ጉዞን የሕዝብ ስሜት ሳቢ እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

የሳይንስ ልቦለድ ደራሲው ሊንግ ቼን የቻይና ሴቶች ጨረቃን በመርገጥ ኅዋ ውስጥ በመውለድ የመጀመሪያዎቹ ሲሆኑ ለማየት እንደሚፈልጉ መናገራቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ምንጩን በመጥቀስ ዘግቧል።

ኅዋን ከ49ዓመታት በፊት በመጎብኘት በዓለም የመጀመሪያዋ ጠፈረተኛ የቀድሞዋ ሶቪዬት ኅብረት ዜጋ ቫሌንቲና ቴሬሽኮቫ መሆኗ ይታወቃል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 252 guests