አይ ሲ ሲ የሎራ ባግቦን ቀጠሮ አስተላለፈ
አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 11/2004 (ዋኢማ) -ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (ኢንተርናሽናል ክሪሚናል ኮርት-አይሲሲ) በቀድሞው የኮትዲቯር ፕሬዚዳንት ሎራ ባግቦ ላይ የተመሠረተውን በሰው ልጅ ላይ ወንጀል የመፈፀም ወንጀል (ክራይም አጌይንስት ሂውማኒቲ) ክስ መስማት ለመጀመር የያዘውን ቀጠሮ እ.አ.አ ወደ ነሐሴ 13ቀን2012 ማስተላለፉን የኤኤፍፒ ዘገባ አመለከተ።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ቀጠሮውን ያስተላለፈው በሎራ ባግቦ ጠበቆች ጥያቄ እንደሆነም ተገልጿል።
የቀድሞው የኮትዲቯር ፕሬዚዳንት ሎራ ባግቦ ጠበቆች ቀጠሮው እንዲተላለፍ የጠየቁትየመከላከያ አቅምን ለማጠናከር የሚያስችል ገንዘብ ለማሰባሰብና በቂ ጊዜ እንዲኖራቸው ለማድረግ እንደሆነ አመልክተዋል። በሎራ ባግቦ ላይ የተመሠረተው ክስ መሰማት ሊጀምር የነበረው እ.አ.አ ሰኔ 18 ቀን 2012 ነበር።
ቀኑ የቀድሞው የአይሲሲ አቃቤ ሕግ ሉዊስ ሞሬኖ አካምፖን የተኩት ጋምቢያዊቷ ፋቱ ቤንሱዳ ሥራቸውን በይፋ የጀመሩበት ቀን እንደሆነ ተገልጿል። ፍርድ ቤቱ የ67 ዓመቱ ሎራ ባግቦ ጠበቆች በቂ ዝግጅት ለማድረግ በጠየቁት መሠረት ቀጠሮውን ወደ ነሐሴ አስተላልፎታል።
ባለፈው ኅዳር ውስጥ በኔዘር ላንድስ ከተማ ዘሄግ ውስጥ ለሚገኘው በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ተላልፈው የተሰጡት የቀድሞው የኮትዲቯር ፕሬዚዳንት ሎራ ባግቦ እ.አ.አ ኅዳር 2010 በተካሄደው የፕሬዚዳንት ምርጫ ሽንፈትን ተቀብለው ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ሁከትና ጦርነት ሂደት በደረሰው ጥፋት አራት ዓይነት የወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዋነኛው እንደተጠቀሰው በሰው ልጅ ላይ ወንጀል መፈፀም ነው።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሎራ ባግቦ ለአሸናፊው የወቅቱ ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ሥልጣን ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት በተቀሰቀሰውና አምስት ወራት በዘለቀው ውዝግብና የእርስ በርስ ጦርነት ከ3,000 በላይ ሕዝብ ሕይወት መጥፋቱ ሲታወቅ ብዙ ሕዝብ ለመፈናቀልና ለስደት መዳረጉ ታውቋል።
እ.አ.አ ሚያዝያ 2011 ሎራ ባግቦ በቁጥጥር ስር ውለው ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በበርካታ የቀድሞ ባለሥልጣኖች በቁጥጥር ስር ውለው ፍርዳቸውን እንዲያገኙ ጥረት በመደረግ ላይ እንደሆነ ታውቋል።
| < Prev | Next > |
|---|


