ሊቢያ የአይሲሲ ልዑካን ቡድን አባላትን አሠረች
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2004 (ዋኢማ) - ሊቢያ የቀድሞውን መሪ ሙአማር ጋዳፊን ልጅ ሳይፍ አልኢስላምን ያነጋገረውን የዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ልዑካን ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ማዋሏን የኤኤፍፒ ዘገባ አመለከተ። በአይሲሲ ልዑካን ቡድን አባላት ላይ ምርመራ ለማካሄድ ይቻል ዘንድ በአቃቤ ሕግ ጥያቄ ለ45 ቀናት እንዲታሠሩ መወሰኑን ስሙን ያልገለጸ የአቃቤ ሕግ ጽሕፈት ቤት ባለሥልጣን ማስታወቁ ተገልጿል።
የአይሲሲ ልዑካን ቡድን አባላትን በቁጥጥር ስር ያዋለው የዚንታን አካባቢ ብርጌድ አዛዥ አጅሚ አልአቲሪ የቡድኑ አባላት የተያዙት የቀድሞውን መሪ ሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አልኢስላም በቁጥጥር ስር ውሎ በሚገኝበት ስፍራ ካነጋገሩ በኋላ እንደሆነ ማረጋገጣቸው ተገልጿል። የብርጌድ አዛዥ የአይሲሲ ልዑካን ቡድን አባሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በአቃቤሕግ ትዕዛዝ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። የቡድኑ አራት አባላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ አንድ ቀን በኋላ ወደ እስር ቤት እንዲገቡ መደረጉ ታውቋል።
የሊቢያ ምዕራባዊ ከተማ በሆነችው ዚንታን ውስጥ ከታሰሩት የአይሲሲ ልዑካን ቡድን አባላት መካከል አንዷ ጠበቃ ሜሊንዳ ቴይለር ለሳይፍ አልኢስላም የሚሰጥ ሰነድ ይዛ መገኘቷ ተገልጿል።
በአይሲሲ የሊቢያ ተወካይ የሆኑት አህመድ ጀሃኒ አውስትራሊያዊቷ ጠበቃ ሜሊንዳ ቴይለር ከሳይፍ አልኢስላም ጋር ሰነድ ስትለዋወጥ እጅ ተፍንጅ መያዟን ማረጋገጣቸው ተገልጿል። አህመድ ጀላኒ እንዳመለከቱት ሜሊንዳ ቴይለር የብዕር ቅርፅ ያለው ካሜራና በአሁኑ ጊዜ በመፈለግ ላይ በሚገኘው የሳይፍ አልኢስላም የቅርብ ረዳት በሞሐመድ እስማኤል ለሳይፍ አልኢስላም የተጻፈ ደብዳቤ ይዛ እንደተገኘችም ጨምረው ገልጸዋል። ደብዳቤው ላኪና ተቀባይ ብቻ የሚረዱት በስዕል መልክ የተቀረፀ ኮድ እንደያዘም አህመድ ጀላኒ ገልጸዋል። በሊቢያ ሕግ መሠረት ይህ እንደስለላ እና ከጠላት ጋር ግንኙነት እንደመፍጠር ተደርጐ እንደሚወሰድ ገልጸዋል።
አህመድ ጀላኒ በተጨማሪ እንዳመለከቱት ሄለን አሳፍ የተባለችው ሊባኖሳዊት የጠበቃ ሜሊንዳ ቴይለር አስተርጓሚም በወንጀሉ ተባባሪነት ተፈርጃለች። ሄሌን አሳፍ እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ ለአይሲሲ በመሥራት ላይ እንደምትገኝ ታውቋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ሌሎች ሁለት የአይሲሲ ልዑካን ቡድን አባላት ሩሲያዊው አሌክሳደር ኮዳኮቭ እና ኢስትባን ፔራልታ ሎሲዛ የተባለ ስፔናዊ መሆናቸውን ገልጿል።
የሊቢያ ጊዜያዊ መንግሥት ቃል አቀባይ ከትናንት በስቲያ በሰጠው መግለጫ ደግሞ አይሲሲ በቁጥጥር ስር በዋሉት የልዑካን ቡድኑ አባላት ላይ በገለልተኛ ወገን ለሚካሄደው ምርመራ አስፈላጊው ትብብር እንደሚያደርግ ዕምነት እንዳለው አመልክቷል።
የመንግሥቱ መግለጫ በተጨማሪም የሊቢያና የአይሲሲ ግንኙነት በሊቢያ ብሔራዊ ጥቅም ኪሳራ ላይ ሊመሠረት እንደማይችል ማመልከቱም ተገልጿል። አይሲሲ የተያዙበት የልዑካን ቡድን አባላት በአስቸኳይ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል። በቁጥጥር የዋሉትን አባላት ለማስለቀቅ የሚደራደር አዲስ የአይሲሲ ልዑካን ቡድን ትሪፖሊ መግባቱ ተገልጿል።
የአይሲሲ ልዑካን ቡድን ሊቢያ የገባው በቁጥጥር ስር የሚገኘው ሳይፍ አልኢስላም የሚከራከርለትን ጠበቃ በመምረጥ ረገድ ድጋፍ ለመስጠት እንደሆነ ሲታወቅ ፣ ለመግባት ከአገሪቱ ዋና አቃቤ ሕግ ፈቃድ እንዳገኘም ተገልጿል። አይሲሲ የ39 ዓመቱ ሳይፍ አልኢስላም በሰውልጅ ላይ ከፍተኛ ወንጀል በመፈፀም (ክራይም አጌይንስት ሂውማኒቲ) ተጠያቂ ሆኖ ዘሄግ ውስጥ ለፍርድ እንዲቀርብ የሚፈልግ መሆኑ ታውቋል። ይሁን እንጂ የሊቢያ ጊዜያዊ መንግሥት ሳይፍ አልኢስላም ፍርዱን ማግኘት ያለበት በአገር ውስጥ ነው የሚል አቋም መያዙ ታውቋል።
እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ ሳይፍ አልኢስላምን በቁጥጥር ስር ያዋለው ብርጌድ ሊያመልጥ ይችላል በሚል ስጋት ከዚንታን ወደትሪፖሊ እንዲዛወር አለመፍቀዱ ታውቋል።
| < Prev | Next > |
|---|


