የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሞቃዲሾን ጐበኙ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2004 (ዋኢማ) - ከሃያ ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ሞቃዲሾን ከትናንት በስቲያ ጐብኝተዋል።
በሞቃዲሾ ጐብኝት ያደረጉትም በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳይ ረዳት ሚኒስትር ጆኒ ካርሰን ናቸው። የጆኒ ካርሰን የሞቃዲሾ ጉብኝት ላለፉት ሃያ ዓመታት ጠንካራ መንግሥት በሌለበት ሁኔታ በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ በቆየችው ሶማሊያ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት መፈጠሩን አመላካች እንደሆነ ተደርጐ የተወሰደ መሆኑን የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ ገልጿል።
ባለፈው ታኅሣሥ ውስጥ ባን ኪ-ሙን ሞቃዲሾን በመጐብኘት ከሃያ ዓመታት ወዲህ ሶማሊያን ለመጐብኘት የመጀመሪያው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ እንደሆኑ መገለጹ ይታወሳል። በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ጆኒ ካርሰን ከትናንት በስቲያ ሞቃዲሾ እንደገቡ ከሽግግር መንግሥቱ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር መነጋገራቸውን የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ አረጋግጧል።
ጆኒ ካርሰን በሞቃዲሾ የአጭር ጊዜ ጉብኝት ካደረጉ በኋላ ናይሮቢ ገብተዋል። ናይሮቢ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በሞቃዲሾ ጉብኝት ያደረጉት በዋና ከተማው ውስጥ ከፍተኛ መሻሻል መኖሩን በአካል ተገኝቶ ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን ስለሚዘጋ ጀው ሕገ መንግሥትና ስለመጪው ጠቅላላ ምርጫ ጉዳይ ከሽግግር መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ጋር ለመነጋገር ጭምር እንደሆነ አረጋግጠዋል።
በአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ መሠረት የሽግግር መንግሥቱ መቆያ ጊዜ እአአ በነሐሴ 20 ቀን 2012 ከመፈጸሙ ቀደም ሲል አዲስ ሕገ መንግሥት መዘጋጀትና አዲስ መንግሥትም መመሥረት ይኖርበታል። የሶማሊያ መሪዎች ከዚህ አንፃር ብርቱ ጥረት እንዲያደርጉም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በማሳሰብ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል።
ረዳት ሚኒስትር ጆን ካርሰን ናይሮቢ ውስጥ በሰጡት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ በሞቃዲሾ ከተማና በአካባቢዋ ደህንነትን በማረጋገጥ ረገድ ከፍተኛ እርምጃ መደረጉን አመልክተው፤ በዚህ ረገድ የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ (አሚሶም) ወታደሮች ያደረጉት አስተዋጽኦም ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል።
የአልቃይዳ አካል የሆነው የሶማሊያ አሸባሪ ቡድን አልሸባብ ከሞቃዲሾ እንዲወጣ የተደረገው ባለፈው ነሐሴ ውስጥ እንደሆነ ይታወሳል። ቡድኑ በአሁኑ ጊዜ ከየአቅጣጫው ወታደራዊ ተፅዕኖ እያረፈበት ይገኛል።
ከሞቃዲሾ በቅርብ ርቀት ላይ የምትገኘውንና ለረጅም ጊዜ ተቆጣጥሯት የቆየችውን ከተማ አፍጐየን እንዲሁም ከኪሰማዮ የወደብ ከተማ 60 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ወሳኝ ስፍራ ለቅቆ እንዲወጣ መገደዱም ይህንኑ የሚያመላክት ነው። የኬንያና የኢትዮጵያ ወታደሮች ድጋፍ በታከለበት ሁኔታ የሶማሊያ ሽግግር መንግሥትና የአሚሶም ኃይሎች የሚካሄዱት ወታደራዊ ዘመቻ የአልሸባብን ሕልውና በማጨለም ላይ እንደሆነ ተገል ጿል።
የአሜሪካው ባለሥልጣን ጆኒ ካርሰን የሰሞኑ የሞቃዲሾ ጉብኝት በዋነኝነት ያተኮረው በፖለቲካዊ ሽግግር ሂደቱ ላይ እንደሆነ ተገልጿል። የአውሮፓና የሌሎች ሀገሮች መሪዎችና ባለሥልጣኖችም የሶማሊያ ፖለቲከኞች የሽግግሩን ሂደት እንዲያፋጥኑ እና በሀገሪቱ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት የሚረጋጋበትን ሁኔታ እንዲያመቻቹ በማሳሰብ ላይ ይገኛሉ።
እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ ከትናንት በስቲያ በሞቃዲሾ ጉብኝት ያደረጉት ረዳት ሚኒስትር ጆኒ ካርሰን በአሁኑ ጊዜ ከስምንት በላይ ሀገሮች በሞቃዲሾ ዲፕሎማቲክ ሚሽን ከፍተው ሠራተኞች መመደባቸውን አረጋግጠዋል። ይሁን እንጂ አገራቸው ተመሳሳይ እርምጃ የምትወስድ በትን ጊዜና ሁኔታ አለማመልከታ ቸው ተገልጿል።
| < Prev | Next > |
|---|


