ኢታኖልን ከቤንዚል ጋር በመቀላቀል 20 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ማዳን ተቻለ
አዲስ አበባ ሰኔ 1/2004 (ዋኢማ) - ኢታኖልን ከቤንዚል ጋር በመቀላቀል 20 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ማዳን መቻሉን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ 20 ሚሊየን ዶላሩን ከውጭ ምንዛሬ ማዳን የተቻለው 32 ነጥብ 862 ሚሊየን ሊትር ኢታኖልን ከቤንዚል ጋር በመቀላቀልና ለምግብ ማብሰያነት ማዋል በመቻሉ ነው።
ከተመረተው 32 ነጥብ 8 ሚሊየን ሊትር የኢታኖል ምርት ውስጥ 27 ነጥብ 4 ሚሊየን ሊትሩ ከቤንዚል ጋር ተቀላቅሎ በቤንዚል ለሚሰሩ መኪናዎች ጥቅም ላይ እንዲውል ሲደረግ፤ ቀሪው ለምግብ ማብሰያነትና ለሌሎች አገልግሎቶች እንዲውል ተደርጓል ብለዋል።
በሀገሪቱ የኢታኖል ድብልቅ ስራ ላይ ከዋለበት ከጥቅምት 2001 ዓ.ም ላይ አምስት በመቶ ኢታኖልና 95 በመቶ ቤንዚን ይቀላቀል የነበረው በአሁኑ ወቅት ማለትም ከመጋቢት 2003 ዓ.ም ጀምሮ ወደ 10 በመቶ ኢታኖልና 95 በመቶ ቤንዚል ማሳደግ መቻሉን ገልፀዋል።
ይህም ወደ ውጪ ለቤንዚል መግዣ ይወጣ የነበረን 20 ሚሊየን ዶላር የውጭ ምንዛሬ ወደ ውጪ እንዳይወጣ ማድረግ ያስቻለ መሆኑን አቶ ብዙነህ አስታውቀዋል።
መንግስት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገትና ብሔራዊ ደህንነት ለማረጋገጥ፣ የነዳጅ ዘይት አጠቃቀም ብቃትን ማሳደግና የነዳጅ ዘይት ፍላጎቶችን በአገር ውስጥ በሚመረቱ የሀይል ምንጮች መተካት ከቁልፍ ስትራቴጂዎቹ መካከል አንዱ መሆኑን የገለፁት አቶ ብዙነህ፤ ይህን ለማሳካትም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አመቱ መጨረሻ ላይም ከስኳር ተረፈ ምርት የሚገኘውን የኢታኖል ምርት ወደ 100 ሚሊየን ሊትር ለማሳደግ እንደታቀደ ገልፀው፤ ለዚህ ተግባራዊነትም ወንጂ ሸዋ፣ መተሃራ፣ ፊንጫ፣ ተንዳሆና ሌሎች የስኳር ፋብሪካዎች ኢታኖል ማምረት እንዲጀምሩ የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ ነው ብለዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


