ቬነስ ፀሐይን አቋርጣ ወደ ምህዋሯ ስታመራ በአዲስ አበባም ታየች
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1፣ 2004 (ዋኢማ)- ቬነስ ፕላኔት ከ105 አመታት በኋላ ፀሐይን አቋርጣ ወደ ምህዋሯ ስታመራ በአለማችን በተለያዩ ሀገራት ታይታለች፡፡
ደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ መካከለኛው ምስራቅ እና ምስራቅ አፍሪካ ፕላኔቷ ከታየችባቸው ሀገራት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
በአዲስ አበባም ግንቦት 29/2004 ዓ.ም ከጠዋቱ 1፡25 አካባቢ ጀምሮ እንዲሁም ረፋዱ ላይ ከ15 እስከ 18 ለሚሆኑ ደቂቃዎች ታይታለች፡፡
በእንጦጦ አስትሮኖሚካል ኦብዘርቫቶሪና ስፔስ ሳይንስ የጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን በላይ ክስተቱ በ105 ዓመታት የሚፈጠር ቢሆንም ከዛሬ ስምንት አመታት በፊት ተመሳሳይ ክስተት እንደነበር ገልፀዋል፡፡
ሌሎችም ፕላኔቶች ፀሐይን አቋርጠው ወደ ምህዋራቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዳለ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ክስተቶቹ ዘመኑ ባፈራቸው አጉሊ መሳሪያዎች እንደሚታዩ አስረድተዋል፡፡
ቬነስ በቀላሉ ልትታይ በመቻሉ ክስተቱን ለመከታተል አስችሏል ማለታቸውንም የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዘግቧል፡፡
በአጠቃይም ክስተቱ በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ ምንም ዓይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንደማያመጣ ይልቁኑም በዩንቨርስ ላይ እያደረገ ያለውን ምርምር ያግዛል ብለዋል፡፡
ከዚህ በኋላ ይላሉ ዶክተሩ ቬነስ ፀሐይን አቋርጣ ስታልፍ ለማየት 105 አመታትን መጠበቅ የግድ ነው፡፡
ቬነስ የተሰኘችው ፕላኔት ከፀሐይ ባላት ርቀት በ2ኛ ደረጃ ላይ ነው የምትገኘው፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


