በናይጄሪያ በአውሮፕላን አደጋ በርካታ ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ግንቦት 29/2004 (ዋኢማ) - በናይጄሪያ ትልቁ ከተማ ሌጎስ ባለፈው እሁድ ምሽት በደረሰው የአውሮፕላን አደጋ ሳቢያ ከ150 በላይ ሰዎች መሞታቸውን የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡ አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በርካታ ሕዝብ ተሰብስቦ በነበረበት ቦታ ላይ በመሆኑ ጉዳቱን እጅግ አስከፊ አድርጎታል፡፡ ይሄው የንግድ አውሮፕላን የሆነው ዳና ኤር የተከሰከሰበት ምክንያት እስካሁን በግልጽ አልታወቀም፡፡

አውሮፕላኑ ከተከሰከሰ በኋላ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት የእሳት አደጋ ተከላካዮችና ፖሊሶች ከፍተኛ ርብርብ ማድረጋቸው ነው የተገለጸው፡፡

የናይጄሪያ ሲቪል አቬዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሀሮልድ ዴሙሪን እንደገለጹት፤ የአውሮፕላኑ ተሳፋሪዎች በሙሉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ 153 ተሳፋሪዎቹ የሚጓዙት ከናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ወደ ሌጎስ ነበር፡፡

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የአውሮፕላኑ አብራሪ አውሮፕላኑ ከመከስከሱ ቀደም ብሎ ሌጎስ ላለው መቆጣጠሪያ ክፍል የሬዲዮ መልእክት አስተላልፎ ነበር፡፡ የመከላለከያ ባለሥልጣናት እንደገለጹት፤ አውሮፕላኑ ከመከስከሱ በፊት በወቅቱ የሞተር ችግር አጋጥሞታል፡፡

የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች በአነፍናፊ ውሻዎች በመታገዝ አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት አካባቢ በህይወት የተረፈ ሰው እና ሬሳ ፍለጋ ጀምረዋል፡፡ የነፍስ አድን ሠራተኞች አደጋው በተከሰተበት አካባቢ በመሬት ውስጥ የተቀበሩ ሰዎች ይኖራሉ የሚል ስጋት አድሮባቸዋል፡፡
የናይጄሪያ ቀይ መስቀል ባቀረበው ሪፖርት መሠረት የ48 ሰዎች አስከሬን በቁፋሮ ተገኝቷል፡፡
ከዚህ በኋላም በቁፋሮ የበርካታ ሰዎች አስከሬን ይገኛል የሚል ግምት አሳድሯል፡፡
‹‹አደጋው የደረሰው በቤቶች አካባቢ በመሆኑ በርካታ ሰዎች ሞተዋል የሚል ፍራቻ አለ›› በማለት ነው የናይጄሪያ ናሽናል ኢመርጀንሲ ማኔጅመንት ኤጀንሲ ቃል አቀባይ ዩሻኣ ሹአቢ የተናገሩት፡፡

ባለስልጣናት እንደገለጹት፤ በአካባቢው ከሚገኙ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ክሬን በመዋስ የወዳደቁ ትልልቅ ስብርባሪዎች እንዲነሱ እየተደረገ ነው፡፡ በአውሮፕላኑ ውስጥ የቀረ ነገር ካለ ለማወቅም ብረታብረትን የመቁረጥ ሥራ እየተከናወነ ነው።

የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ጉድላክ ጆናታን አደጋው በደረሰበት ስፍራ ለ20 ደቂቃዎች በመቆየት የደረሰውን አደጋ ስፋት ለመመልከት ችለዋል፡፡ እሳቸው እንዳሉት የአውሮፕላኑ መከስከስ የናይጄሪያ አቬሽን ያለበትን ክፍተት ያመለክታል፡፡

« በዚች ሀገር ላይ የዚህ ዓይነቱ አደጋ ዳግም አይከሰትም›› ብለዋል - ፕሬዚዳንቱ።
አደጋው ለሀገሪቱ ባለፉት ሃያ ዓመታት ውስጥ ያጋጠመ እጅግ አስከፊ አደጋ ተብሎለታል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት ከአሁኑ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ቦይንግ ኤም ዲ83 አውሮፕላን በሞተሩ ውስጥ ወፍ በመግባቷ ችግር ገጥሞት እንደነበር የአቬዬሽኑን መረጃ በመጥቀስ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 198 guests