ኪነ ጥበብን ለመልካም ገፅታ ግንባታ ማዋል እንደሚገባ ተጠቆመ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ግንቦት 16 2004 (ዋኢማ) - ኪነ ጥበብን በሚገባ በማሳደግ የአገሪቱን መልካም ገፅታ መገንባት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ማኅበር ትናንት በግዮን ሆቴል «ኪነ ጥበብ ለሀገሪቱ ሕዳሴ መልካም ገጽታ ግንባታ ያለው ሚና» በሚል ርዕስ ባካሄደው ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ታደለ ይመር እንደገለጹት፤ ባለፉት ዘመናት ሀገሪቱ ትታወቅበት የነበረው ገፅታ ሊለወጥ ይገባዋል።

«ኪነ ጥበብ በታለመለትና በታቀደለት መስመር እንዲሄድ ከተደረገ የአገር መልካም ገፅታን በመገንባትና መልካም ጎኑን በማስተዋወቅ ረገድ እጅግ ታላቅ ተግባር ማከናወን ይቻላል» ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ የሀገራችንን ሕዳሴ ማብሰር በዓለም ዘንድ ያለንን መልካም ያልሆነ ገፅታ ለመቀልበስና መልካም ገጽታን ለመገንባት ትልቅ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

ማኅበራቸው ቀደም ሲል በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ስለ ሀገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ በግልፅ እንዲያውቁ ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በዓውደ ጥናቱ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሰላምና ልማት ዓለም አቀፍ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ስብሀት ነጋ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ በኪነ ጥበብ በሚተላለፈው መልዕክት መልካሙን በማወደስ መጥፎውን በማወገዝ ሀገርን መገንባት ይቻላል።

ባለፉት ዘመናት በሀገሪቱ ውስጥ በርካታ ጥሩ ነገሮች የመሠራታቸውን ያህል የሀገርን ገፅታ የሚያጐጽፉ መጥፎ ነገሮች መከሰታቸውንም አመልክተው፤ ይህን የጐደፈ ገጽታ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን እውቀት በማዳበር በኪነ ጥበብ መቀየር እንደሚቻል ተናግረዋል።

ካለፉት ሥርዓቶች የወረስናቸውን «ጠባብነት፣ ትምክህተኝነት፣ ጦርነትና መናናቅን»ለማስቀረት ኪነ ጥበብ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አቶ ስብሐት ጠቁመው፤ «በኪነ ጥበብ ይህን ማስወገድና በሕብረተሰቡ ውስጥ መልካም ነገር ማስረፅ ይቻላል» ብለዋል።

በዓውደ ጥናቱ ላይ ጥናታዊ ፅሑፍ ያቀረቡት አቶ አበበ ዓይነቴ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኪነ ጥበብ ለሀገራችን መልካም የገፅታ ግንባታ የተጫወተው ሚና የጐላ አይደለም። የመልካም ገፅታ ግንባታ የመንግሥት ሥራ ብቻ ተደርጐ ይወሰዳል። «ይሁን እንጂ ኪነ ጥበብ ለሀገር መልካም ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል» ብለዋል።

የሀገሪቱ ኪነ ጥበብ በተለይም የፊልም ኢንዱስትሪውን ለሀገር መልካም ገፅታ ግንባታ ለማዋል ያሉ ምቹ ሁኔታዎችና ተግዳሮቶችን በጥናታቸው አመልክተዋል። እንደ አቶ አበበ ገለፃ ለመልካም ገፅታ ግንባታ ተግዳሮቶች ተደርገው ከሚወሰዱ ነጥቦች አንዱ ሙስና የዕድገት መሰላል ተደርጐ መወሰዱ ይገኝበታል።

ለገፅታ ግንባታ መልካም አጋጣሚዎች ብለው ካነሷቸው መካከል የእድገትና ትራንስፎርሜሽኑ ዕቅድ ሙስናን መዋጋት እንደቁልፍ ነጥብ ማስቀመጡ መልካም አስተዳደር ማዕዘን ድንጋይ መፍጠሩ እቅዱ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚለውጥ መሆኑ ተጠቃሾች ናቸው።

የዓውደ ጥናቱ ተሣታፊዎች በሰጡት አስተያየት የሀገሪቱ ኪነ ጥበብ በመልካም ገፅታ ግንባታ ላይ እስከአሁን ብዙ አስተዋፅኦ አለማድረጉን አመልክተዋል። ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶችን አንስተዋል። ከእነዚህም ውስጥ የሰለጠነ ባለሙያ የሚያፈሩ ትምህርት ቤቶች አለመስፋፋት ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አለመኖር፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት አለመስጠቱና የታክስ ጫና መኖሩ እንዲሁም ተባብሮ አለመሥራት በዋናነት ያነሷቸው ነጥቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ሕዳሴ ማኅበር መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሲሆን በጥቂት ፈቃደኞች ተመስርቶ አሁን በሀገር ውስጥና በውጭ በርካታ አባላት ያሉት መሆኑ ታውቋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ነው።



  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 310 guests