የአፍሪካ የአየር ንብረት ፖሊሲ ማዕከል አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ዝግጁ መሆን አለባት በሚል ውይይት አካሄደ
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16/2004 (ዋኢማ) - አፍሪካ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ላሳየችው የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት የመሰረተ ልማት አውታር ከግማሽ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ይሸፍናል፡፡
ይህም ዘርፍ በሚቀጥሉት ዓመታት በአህጉሪቱ አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ላይ ከዚህም የበለጠ ድርሻ እና ሚና እንደሚኖረው የዓለም ባንክ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እምነት ነው፡፡
በአፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ግዙፍ ድርሻ እንደሚኖረው የሚታመነው ይኸው ዘርፍ ግን ወቅታዊ ተግዳሮቶች እየገጠሙት እንደሚገኙ ይነገራል፡፡ ከዚህም ውስጥ የአፍሪካን አካባቢያዊ ትስስርን በመሰረተ ልማት እውን ለማድረግ እና አፍሪካውያን ዜጐች አገልግሎቱን የሚያገኙት በተዘዋዋሪ በውድ ዋጋ መሆኑ ተጠቃሽ ነው፡፡
ከሁሉም ችግሮች በላይ ግን በየጊዜው የሚቀያየረው የአየር ንብረት አደጋ ነው፡፡ በውኃ ሙላት መንገድን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች መጎዳታቸው አይቀርም፡፡ በውኃ እጥረትም እንዲሁ የኃይድሮ ፓወር ፕሮጀክቶች ስራ ከመስተጓጎል አይድንም፡፡
የአፍሪካ የአየር ንብረት ፖሊሲ ማዕከል አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ዝግጁ መሆን አለባት በሚል መነሻ በአዲስ አበባ ተወያይቷል፡፡ በዚሁ ወቅት እንደተመለከተው የመሰረተ ልማት አውታሮች የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ሚናቸው የጐላ ነው፡፡ ጤናማ የአየር ንብረትም ለመሰረተ ልማት አውታሮች ሕልውና ነው ተብሏል፡፡
በቦስተን የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተመራማሪ ኬኔዝ በትሬቤክ እንደሚሉት በኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ያሉት እንደ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የነገውንም የአየር ንብረት ለውጥ ችግር ከግምት ውስጥ ያስገቡ ናቸው፡፡
በአፍሪካ መሰረተ ልማት ላይ የሚውለውን ሀብት ከብክነት በመታደግም እስከ 17 ቢሊዮን ዶላር ማዳን እንደሚቻልም የዓለም አቀፍ የምጣኔ ሀብት ተመራማሪዎች ይገልፃሉ፡፡ ይህም በዘርፉ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ክፍተት ለመሙላት አጋዥ ነው፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


