ኔቶ ከአፍጋኒስታን የመውጫ ዕቅድ አፀደቀ

  • PDF

በአሜሪካ ቺካጐ ከተማ ውስጥ የተካሄደው የሰሜን አትላንቲክ መከላከያ ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የመሪዎች ጉባኤ ለአፍጋኒስታን መንግሥት ፀረ-ታሊባን ጦርነት ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኘው የድርጅቱ ኃይል የውጊያ አመራሩን እ.አ.አ በ2013 አጋማሽ ላይ ሙሉ በሙሉ ለአገሪቱ ጦር ኃይሎች ለማስረከብ የወጣውን ዕቅድ ማፅደቁ ተገለጸ። ባለፈው እሁድና ሰኞ በቺካጐ ከተማ ውስጥ የተካሄደው የኔቶ መሪዎች ጉባኤ በአፍጋኒስታን ያሰማራውን ድጋፍ ሰጭ ኃይል እ.አ.አ በ2014 መጨረሻ ለማስወጣት የወጣውን ዕቅድም መደገፉ ተረጋግጧል።

ለአፍጋኒስታን መንግሥት ድጋፍ በመስጠት ላይ የሚገኘው የኔቶ ኃይል እ.አ.አ በ2014 መጨረሻ የሚወጣ ቢሆንም አገሪቱ የአሜሪካና የሌሎች የኔቶ አባል አገሮች ድጋፍ እንደማይለያት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በጉባኤው ፍጻሜ ላይ በሰጡት መግለጫ አመልክተዋል። ባለፈው እሁድና ሰኞ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ሃያ ስምንቱን የኔቶ አባል አገሮች መሪዎች ጨምሮ 50 መሪዎች መካፈላቸው ተገልጿል።

የኔቶ ዋና ፀሐፊ አንድርስ ፎግ ራስ ሙሰን በሰጡት መግለጫ ደግሞ የኔቶ ኃይል ከወጣ በኋላ ለአፍጋኒስታን ጦር ኃይሎች የሚያስፈልገውን በየዓመቱ የአራት ቢሊዮን ዶላር ያህል ድጋፍ ለመሸፈን በርካታ የኔቶ አባል አገሮች ፈቃደኛነ ታቸውን እንዳመለከቱ ገልጸዋል። በተለይ አሜሪካ ከእዚህ ወጪ ከፍተኛውን ድርሻ እንደምትሸፍን ተገምቷል።

ዋና ፀሐፊው የፓኪስታን መንግሥት 24 ወታደሮቹ በወሰን አካባቢ በኔቶ ኃይሎች መገደላቸውን ምክንያት በማድረግ በፓኪስታን በኩል ወደአፍጋኒስታን ለኔቶ የሚተላለፈው ትጥቅና ስንቅ እንዳይተላለፍ ያደረገው ውሳኔ እስከአሁን እንዳልተነሳ አመልክተው፤ ዕገዳው በኔቶ ላይ ያደረሰው ጉዳት ግን የሚጋነን እንዳልሆነ ገልጸዋል። የፓኪስታን መንግሥት ዕገዳውን ያነሳል የሚል ግምት እንዳለ ተገልጿል። የፓኪስታን መንግሥት ዕገዳውን የማንሳት ፍላጐት ያለው መሆኑን በኔቶ የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት ፕሬዚዳንት አሲፍ ዓሊ ዛርዳሪ መመልከታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ገልጿል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 432 guests