ፀጥታ ምክር ቤት በየመን የተፈፀመውን አደጋ አወገዘ

  • PDF

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16/2004 (ዋኢማ) - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ በየመን ዋና ከተማ ሰንአ ውስጥ የተፈፀመውን የሽብር ጥቃት በጥብቅ አወገዘ። በአንድ የየመን አልቃይዳ ቡድን አጥፍቶ ጠፊ እንደተፈፀመ በተነገረለት የፈንጂ አደጋ ከ90 በላይ ወታደሮች ሲገደሉ ሌሎች 222 ወታደሮች የተጐዱ መሆናቸውን ቢቢሲ የአገሪቱን መከላከያ ሚኒስቴር ባለሥልጣኖች ጠቅሶ አመልክቷል።

አደጋው ለአገሪቱ ብሔራዊ ቀን አከባበር በዋዜማው በወታደራዊ ሰልፍ ልምምድ ላይ በነበሩ ወታደሮች ላይ የተፈፀመው ተመሳሳይ የወታደር ልብስ ለብሶ በተቀላቀለ በየመን አልቃይዳ ቡድን አጥፍቶ ጠፊ እንደሆነ ተረጋግጧል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤት አደጋው ከተፈፀመ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ባወጣው መግለጫ የተፈፀመውን አሰቃቂ አደጋ አውግዞ በማናቸውም መልክ የሚከሰትን የሽብር ጥቃት በፅናት የሚዋጋ መሆኑን ገልጿል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙንም የሽብር ጥቃቱን በግል አውግዘው የመናውያን በመላ ሁከትን ለማስወገድና ፖለቲካዊ የሽግግር ሂደቱን ለማሳካት በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚኖርባቸው አስገንዝበዋል። የሽብር ጥቃቱ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማንና የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ሆላንድን ጨምሮ በበርካታ መሪዎች መወገዙ ተገልጿል።

ትናንት በተከበረው የአገሪቱ ብሔራዊ ቀን ዋዜማ የተፈፀመው አደጋ በራሱ አጥፍቶ ጠፊ አማካይነት መከናወኑን በማመልከት የየመን አልቃይዳ ቡድን ኃላፊነቱን መውሰዱን የቢቢሲ ዘገባ ጨምሮ ገልጿል።
የየመን ፕሬዚዳንት አብድራቦ ሐዲ ማንሱር ከትናንት በስቲያ የተፈፀመው አደጋ መንግሥታቸው በአሸባሪዎች ላይ የሚያካሂ ደውን የጥቃት ዘመቻ አጠናክሮ ከመቀጠል ሊያግድ እንደማይችል። አመልክተዋል። ፕሬዚዳንቱ በማያያዝም በሽብርተኝነት ላይ የተከፈተው ጦርነት የየመኑ አል ቃይዳ ቡድን እስከሚደመሰስ ድረስ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ባለፈው የካቲት ከቀድሞው ፕሬዚዳንት ዓሊ አብዱላ ሳሌህ የተረከቡት አብድ ራቦ ሐዲ ማንሱር የየመኑን አልቃይዳ ቡድን የአለመረጋጋት ሁኔታ ሲታይባቸው ከቆዩት የአገሪቱ ደቡባዊና ምሥራቃዊ ክፍሎች ለማፅዳት ቃል መግባታቸው ተገልጿል። በየመን ሲካሄድ የቆየው ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በፈጠረው ሁኔታ በመጠቀም አንሳር አልሻሪያ የተባለው የየመን አልቃይዳ ቡድን ካለፈው ዓመት ጀምሮ አብያን የተባለውን ደቡባዊ ክፍለ ሀገር መቆጣጠሩ ተገልጿል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 155 guests