የአፍሪካ የፓርላማ አባላት የሚሊኒየም የዕድገት ግቦችን ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ
አዲስ አበባ፤ ግንቦት 14/2004 (ዋኢማ) - የአፍሪካ የፓርላማ አባላት የተባበሩት መንግስታት የምዐተ ዓመቱን የልማት ግቦችን እውን ለማድረግ ይቻል ዘንድ ሁሉም ወገን በተቀናጀ መልክ ጥረትና ርብርብ እንዲያደርግ ጥሪ አቀረቡ፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን ለዋልታ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦችን ለማሳካት የአፍሪካ የፓርላማ አባላት የጋራ መድረክና በተባበሩት መንግስታት የሚሊኒየም ግቦች አስፈጻሚ አዘጋጅነት ከግንቦት 13- 17/2004ዓ.ም በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ስብሰባ ይካሔዳል፡፡
እንደ መግለጫው የአህጉራዊው ስብሰባ ዋነኛ የመወያያ ርዕስ በሚሊኒየሙ ለማሳካት ተለይተው የተቀመጡ የልማት ግቦችን እንዴት በተሻለ ፍጥነት ለማሳካት የፓርላማ አባላት ሚናና በቀጣይ ከ2015 በኋላ ስለሚኖር የዕድገት አጀንዳ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የሚሊኒየም ግቦች አስፈጻሚ - የአፍሪካ አህጉር ዳይሬክተር ሚስተር ቻርለስ አቡግሬ እንደገለጹት የጉባዔው ዋነኛ ዓላማ
“በሚሊኒየሙ የተቀመጡ የዕድገት ግቦች በቀሪው ጊዜ መሳካታቸውን ለማረጋገጥ በአፍሪካ ፓርላማ አባላት ዘንድ ተነሳሽነት እንዲፈጠርና ለስኬቱም ከፍተኛ ግፊት እንዲያደርጉ፤ እንዲሁም ተለዋዋጭ የሆነውን የዓለም ኢኮኖሚና የአስተዳደር ሁኔታ በመገንዘብ ከ2015 በኋላ በሚሊኒየሙ የተቀመጡ የእድገት ግቦችን የሚተካውን ዓለም ዓቀፍ የዕድገት አጀንዳ ከመቅረጽ አንጻር ግንባር ቀደም ተዋነይነታቸውን ለማረጋገጥ ነው፡፡ ” ከዚህም በተጨማሪ ሚስተር አቡግሬ እንደአብራሩት፣ “ በጉባዔው ላይ የክፍለ አህጉሩንና የብሔራዊ ፓርላማን፣የሲቪል ማኅረሰቡን፣የተባበሩት መንግስታትንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ከ200 በላይ ተሳታፊዎች ይገኛሉ፡፡”
ጉባዔውን በጋራ የአዘጋጁት የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣ በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ቋሚ ተጠሪ ጽ/ቤትና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ቋሚ ተጠሪ ናቸው፡፡ ከዚህም ሌላ ይህንን ጉባዔ ለማዘጋጀት የጋራ ብልጽግና አገሮች ኅብረት፣ በናይጄረያ በተካሄደው ጠቅላላ ስብሰባ ላይ ተመረጠው የሚሊኒየም ዕድገት ግቦች ኮሚቴ፣ የፓርላማዎች የጋራ ጥምረት፣የአፍሪካ አንድነት ኮሚሽን፣በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ቋሚ ተጠሪ አስተባባሪና በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሚስተር ኢጅን ኦዉሱ በበኩላቸው ስብሰባውን አስመልክቶ ሲናገሩ “በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የተለያዩ አካላት የሚሊኒየም የዕድገት ግቦች ወሳኝ ምዕራፍ ላይ በደረሰቡት ወቅት፣በአንድ በኩል በአፍሪካ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት በሚመዘገብበትና በዲሞክራሲያዊ ሂደቶች ላይ ከፍተኛ መሻሻል በሚታይበት ወቅት፤በሌላ በኩል ደግሞ በኅብረተሰባችን ውስጥ በአንዳንድ ሰብዓዊ ዕድገቶች ላይ ከረር ያሉ አሉታዊ ሁኔታዎች ሲፈፀሙ በምናይበት ወቅት ይህንን ስብስባ በማዘጋጀታቸው ከፍተኛ ደስታ ይሰማቸዋል፡፡ወደ ሚሊኒየሙ የዕድገት ግቦች ለመድረስ የምንሻ ከሆነ ዛሬውኑ በአስቸኳይ
ወደተግባር መግባት አለብን፡፡ይህንን ለማሳካት ደግሞ የፓርላማ አባላቶቻችን ግንባር ቀደም ተዋነይ እንዲሆኑ እንፈልጋልን” ማለታቸውን መግለጫው ጠቁሟል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


