በአዲስ አበባ የኮብል ድንጋይ ንጣፍ ሥራን ለማገዝ ህብረተሰቡ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉ ተገለፀ
አዲስ አበባ ፤10 2004 (ዋኢማ) - በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ ክፍለ ከተማዎች እየተካሄደ ያለውን የኮብል ድንጋይ ንጣፍ ሥራ ለማገዝ ህብረተሰቡ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር አስታወቀ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የሚመራ ቡድን በከተማዋ በኮብል ድንጋይ ንጣፍ ሥራ አበረታች አፈጻጸም ያሳዩትን የጉለሌ ፤ ኮልፌና ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማዎችን ሰሞኑን ጎብኝቷል።
ከንቲባ ኩማ ደመቅሳ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለፁት ዘንድሮ በከተማዋ እየተካሄደ ያለውን የኮብል ድንጋይ ንጣፍ ሥራ ለማገዝ ነዋሪዎች ከ339 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አድርገዋል።
እንደ ከንቲባው ማብራሪያ በበጀት አመቱ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከ139 ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ የኮብል ድንጋይ ለማንጠፍ ታቅዶ ከ119 ኪሎ ሜትር በላይ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት በቅቷል። የ 10 ኪሎ ሜትር መንገድ ሥራም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የኮብል ድንጋይ ማንጠፍ ሥራ ለበርካታ ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ከንቲባ ኩማ በዘርፉ በወር እስከ 7 ሺ ብር ያህል ገቢ የሚያገኙ ሰዎች እንዳሉም አብራርተዋል።
ከኮብል ድንጋይ ማንጠፍ ሥራ ተነስተው ካፒታላቸውን በማሳደግ ወደ ሌላ የሥራ ዘርፍ ለመሸጋገር ለመንግሥት ጥያቄ እያቀረቡ ያሉ ግለሰቦች እንዳሉ ሁሉ በተቃራኒው በከፍተኛ ደረጃ ሥራን የመናቅ አመለካከት እንዳለ ጠቁመው የአመለካከት ለውጥ ለማምጣት አሁንም ከፍተኛ ሥራ መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ዘርፉን የበለጠ ለማጠናከር ከወረዳ በታች 789 ያህል ቀጣናዎች ተደራጅተው የየራሳቸውን የልማት ኮሚቴዎች አዋቅረው ህዝቡን እያሳተፉት እንደሚገኙ የጠቆሙት ከንቲባው በከተማዋ አነስተኛ አፈጻጸም ያላቸው ክፍለ ከተማዎችም ሥራቸውን በመገምገም የተሻለ ተሞክሮ ካላቸው ክፍለ ከተማዎች ልምድ መቅሰም እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


