የግንቦት ሃያ 21ኛ ዓመትና የደኢህዴን 19ኛ ዓመት በዓልን አስመልክቶ

  • PDF

ከደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ
ጽህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ

በሀገራችን ለዘመናት ተንሠራፍቶ የቆየው ፀረ-ዴሞክራሲያዊ አገዛዝ የህዝቡን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አፍኖ ለከፋ ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና ዳርጐት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ባለብዙ ብሄር፣ ቋንቋና ሃይማኖቶች መናኸሪያ በሆነችው አገራችን ብዝሀነት ለእድገትና ለጠንካራ አንድነት ምንጭ መሆኑ ቀርቶ ሰዎች በማንነታቸው፣ በቋንቋቸውም ሆነ በሚከተሉት እምነት ሳቢያ ተንቀውና ተዋርደው እንዲቆዩ ተደርጓል።

በየወቅቱ ሲፈራረቁ የነበሩ ገዥዎች በዓይነቱ የከፋ ብሄራዊና መደበኛ ጭቆና በማንሠራፋት እኩል የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት መብቶችንም በመንጠቅ ህዝቦችን ስር ለሰደደ ድህነት፣ ረሃብና ጉስቁልና፣ መላውን አገሪቱን ደግሞ ለጦርነትና ለመበታተን አደጋ ዳርገው እንደቆዩ የሚታወስ ነው። ይሁንና ይህንኑ አስከፊ ስርዓት ከሃገራችን ህዝቦች ጫንቃ በመግፈፍ ሰላም፣ ዴሞክራሲንና ልማትን እውን ለማድረግ በማለም በተበታተነ መልኩ ሲካሄድ የነበረውን የህዝቦችን ትግል ወደተደራጀ ኃይል ያሸጋገረውና የኢትዮጵያን ህዝቦች የዘመናት ብሶት ያነገበው ኢህአዴግ ህዝቡን አንቀሳቅሶ በከፈለው መስዋእትነትና እልህ አስጨራሽ ትግል የዛሬ 21 ዓመት ግንቦት 20 ቀን የነፍጠኛው ስርዓት የመጨረሻው ምዕራፍ ወኪል የነበረውን የደርግ አገዛዝ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመገርሰስ በሀገራችን አዲስ የሰላም የዴሞክራሲና የልማት ምህዳር እንዲፈጠር አስችሏል።

ከግንቦት 20 የድል ፍሬ ተቋዳሽ የሆኑት የደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦችም ከላያቸው ላይ እጅጉን በከፋ መልክ ተንሰራፍቶ የቆየው ብሄራዊና መደባዊ ጭቆና በመገፈፉ በድሉ ማግስት የተደራጀ ፖለቲካ ትግል ለማካሄድ የሚያስችላቸውን የየብሄረሰብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶችን በማደራጀትና በ1985 ዓ.ም እነዚህን ከ21 የማያንሱ ብሄራዊ ድርጅቶችን በጋራ በማሰባሰብ ክልላዊ የጋራ ግንባር የሆነውን ደኢህዴግን በመመስረት በኢህአዴግ አገራዊ አመራር ስር ተሰባስበው ትግላቸውን ለመጀመር ችለዋል። የ21 ድርጅቶች ስብስብ የነበረው ደኢህዴግ በሂደት በተሃድሶ እንቅስቃሴ በመታገዝ ከብሄራዊ ድርጅቶች ስብስብነት ወደአንድ ክልላዊ ንቅናቄ በመሸጋገር ጠንካራ ክልላዊ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ማህበረሰብን የመፍጠር ግብ ይዞ ለመንቀሳቀስ በሚያስችለው አኳኋን በ1995 ዓ.ም አደረጃጀቱን ከቀየረ ወዲህ በክልሉ ታላላቅና አመርቂ የሚባሉ አብዮታዊ ድሎች ሲመዘገቡ ቆይተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደኢህዴን/ ክልሉን በመራባቸው ባለፉት ዓመታት የግንቦት 20ን የድል ቋያ በመላ ክልሉ በላቀ መንገድ በማቀጣጠል መላ የደቡብ ህዝቦች ብሄራዊና መደባዊ ጥቅሞቹ ተሟልተው እንዲከበሩለት አድርጓል። የክልሉ ብሄሮችና ብሄረሰቦች ከምንም በላይ ራሳቸውን የሚያስተዳድሩበትን የፖለቲካ ስልጣን ባለቤትነት እውን በማድረግ በክልሉ ጠንካራና በዓይነቱ ልዩ የሆነ ያልተማከለ ፌደራላዊ አስተዳደር ስር እንዲሠድ በማድረግ በሂደቱም መላውን ህዝብ ያንቀሳቀሰና ተጠቃሚ ያደረገ ልማትን እውን ለማድረግ ችሏል። በክልሉ የሚገኙ 56 ብሄረሰቦች በየአካባቢያቸው በቋንቋቸው የመማርና የመዳኘት፣ ባህላቸውንና ወጋቸውን የማሳደግ፣ እንደክልል ደግሞ ከጋራ አንድነት የሚገኘውን ጥቅም በተጨባጭ እየተረዱ እንዲመጡ በማድረግ፣ በተለይም ደግሞ በሀብት ክፍፍልና በጋራ ጥቅሞች ዙሪያ ብሄራዊ አድልዎና መበላለጥ እንዳይፈጠር ባገኙት ህገ-መንግስታዊ ዋስትና ተጠቅመው በጋራ የመሠረቱት ክልል የውበታቸውና የአንድነታቸው መገለጫ መሆኑን ተረድተው በብዝሃነት ምሰሶ ላይ የተተከለ ጠንካራና ምናልባትም ለመላው ዓለም ምሳሌ የሚሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲፈጥሩ አስችሏል።

ደኢህዴን ባለፉት ፈታኝ የትግል እና የድል አመታት የህዝቡ ፖለቲካዊ መብቶች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አግኝተው እንዲያብቡ ከማድረጉም ባሻገር በክልሉ ፈጣን፣ ቀጣይነት ያለውንና ሁሉንም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ልማትን በማረጋገጥ ታሪካዊ ተልዕኮውን በድል እየተወጣ ይገኛል።

የደቡብ ህዝቦች በንቅናቄው አብዮታዊ ዴሞክራሲዊ አመራር ተመርተው ባካሄዱት ልማታዊ ትግል በክልሉ የትምህርት፣ የጤና፣ የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ መንገድና ሌሎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አገልግሎቶች ተደራሽነትና ተጠቃሚነት እመርታ ታይቶበታል። ለአብነት ያክል በክልሉ የዛሬ 21 ዓመት ከ17 በመቶ በታች የነበረው የትምህርት ሽፋን ዛሬ ጥቅል ተሳትፎ ከመቶ በመቶ የዘለለ ሲሆን በየቀበሌው አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለማዳረስ በተሰራው ሥራም 5ሺህ498 ትምህርት ቤቶች ተገንብተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ። በደርግ ውድቀት ማግስት በጣት የሚቆጠሩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በነበሩበት ክልላችን ባሁኑ ወቅት ከ246 የሚበልጡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከፍተው አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ሲሆን ከፌዴራል መንግስት ጋር በመተጋገዝ በተያዘው ዕቅድ መሠረትም ከፍተኛ ትምህርትና ሥልጠናን ለማስፋፋት በተደረገዉ ርብርብ ደግሞ በተለያዩ መስኮች የሚያሰለጥኑ በርካታ ኮሌጆችና 7 ዩኒቨርሲቲዎች ተከፍተው የክልሉ ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆን ተደርጓል። የጤና አገልግሎትን ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተደረገው መጠነ ሰፊ ርብርብ 3ሺህ603 የጤና ኬላዎችን በመገንባትና በነዚህ ተቋማት የጤና ኤክስቴንሽን አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን አሰልጥኖ በማሰማራት በዓለምአቀፍ ደረጃ አድናቆትን ያተረፈ የጤና ኤክስቴንሽን ሥርዓት ለመዘርጋት የተቻለ ሲሆን  በየ25 ሺህ ህዝብ ቁጥር የጤና ጣቢያ ለማዳረስ በተሰራ ሥራም በደርግ ውድቀት ማግስት 28 የነበረው የጤና ጣቢያ ቁጥር በአሁኑ ወቅት በቅርብ ተጠናቀው ለአገልግሎት የሚበቁትን ጨምሮ  በድምሩ 674 እንዲደርስ ተደርጓል። የዛሬ 21 ዓመት ከ5 የማይበልጥ ሆስፒታል በነበረበት በዚሁ ክልል ዛሬ 54 በግንባታ ላይ ያሉትን ጨምሮ 74 እንዲደርስ ተደርጓል።

ኢኮኖሚያዊ ልማትን ለማፋጠን የግብርናው ክፍለኢኮኖሚ በገበያ በተለይም ደግሞ በዓለም ገበያ የሚመራ እንዲሆን በማለም ለክልሉ አርሶአደሮች በተሠጠው ሁለንተናዊ ድጋፍ የክልሉ ምርትና ምርታማነት በፍጥነት እያደገ የሚገኝ ሲሆን በርካታ አርሶአደሮች ከድህነት ተርታ ተላቀው ወደባለሃብት ጎራ የተቀላቀሉበትና በምግብ ዋስትና ችግር ሲሰቃዩ የነበሩ በሚሊዮን  የሚቆጠሩ ቤተሰቦችም ራሳቸውን ወደመቻል የተሸጋገሩበት፣ በጥቅሉ ግብርናችን ከድህነት መገለጫነት ወደሀብታሞች ማፍለቂያነት መሸጋገር የጀመረበትን ሁኔታ እውን ለማድረግ ተችሏል።

በከተሞችም በጥቃቅንና አነስተኛ ስራ ፈጠራ አማካይነት በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ችለው ሌሎች በርካታዎችን የእድሉ ተጠቃሚ ማድረግ የቻሉበት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴና ተጠቃሚነት እየሰፋ የመጣበት ውጤት ተመዝግቧል። በገጠርም ይሁን በከተሞች የተጀመሩ የልማት ተግባራት ንቅናቄው በተሃድሶ እንቅስቃሴ ውስጥ በተራመደባቸው ባለፉት ስምንት ተከታታይ ዓመታት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች የተገኘባቸው ሲሆን ለዘመናት ከላባቸውና ከሃብታቸው ተጠቃሚ ሳይሆኑ የቆዩት የደቡብ ህዝቦች ከድህነት ተላቀው በሀገር ደረጃ በተያዘው ራዕይ መሠረት መካከለኛ ገቢ ላይ የሚደርሱበትን ትክክለኛ ጉዞ አመላካች የሆነ ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል።

ንቅናቄው ባለፉት የትግል ዓመታት ያስመዘገባቸው ድሎችና ውጤቶች አልጋ በአልጋ በሆነ መልኩ የተጎናጸፋቸው አልነበሩም። ይልቁንም የልማታዊ መስመሩን የበላይነት ለማረጋገጥ በአንድ በኩል ልማታዊ ኃይሎችን በማደራጀትና በመገንባት፣ በሌላ በኩል የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦችና ተግባራትን በጽናት በመመከት በልማታዊነትና በኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰቦች መካከል የሚካሄድ ወሳኝ ፍልሚያ ውስጥ በመራመድ የተገኙ ውጤቶች እንጂ።

ደኢህዴን የዘንድሮ ግንቦት 20 በዓልና 20ኛ ዓመት ልደቱን ከመላ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ሆኖ ሲያከብር በአንድ በኩል በሀገር ደረጃ የተነደፈው የ5 ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ለማሳካት በሚካሄደው አገራዊ ርብርብ የጋራ ግንባር በሆነው ኢህአዴግ ጥላ ስር የበኩሉን ጠንካራና ውጤታማ ሚና ለመወጣት የሚጠበቅበት ኃላፊነት ታላቅ መሆኑን በመረዳት፣ በሌላ በኩል በክልሉ ውስጥ ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታውን ወደማይቀለበስበት ደረጃ ለማድረስ ያስቀመጣቸውን አቅጣጫዎች ለማሳካት የሚያስችል ብቁ አመራር ለመስጠት ሰፊ ርብርብ የሚያካሄድበትና በተለይም በገጠርም ሆነ በከተሞች ብቁና አስተማማኝ የልማት ሰራዊት ለመገንባት የሚረባረብበት ዓመት መሆኑ በዓሉን የተለየ ያደርገዋል።

መላ አባሎቻችንም ሆኑ ደጋፊዎቻችን ይህንን የግንቦት 20 የድል ቀንና የንቅናቄውን 19ኛ ዓመት በዓል ሲያከብሩ ባለፉት የድልና የትግል ዓመታት የተመዘገቡና ህዝባችንን ተጠቃሚ ያደረጉ ውጤቶች በንቅናቄውና በህዝባችን የጋራ ትግል የተገኙ መሆናቸውን በመገንዘብ በቀጣይም ንቅናቄውና በንቅናቄው የሚመራው የክልሉ መንግስት የነደፋቸው የ5 ዓመት ዕቅዶች በምልዓተ ህዝቡ የተደራጀ ንቅናቄ እንዲሳኩ ሌትተቀን በየተሠማሩበት መስክ በመረባረብ ድህነትን ለመመንገልና ለሃገራችን የህዳሴ ጉዞ መሳካት በአጭር ታጥቀው እንዲረባረቡ ደኢህዴን ዛሬም እንደትናንቱ ጥሪውን ያቀርባል።

በክልላችንም ሆነ ከክልል ውጪ የሚገኙ ደጋፊዎችና የክልሉ ተወላጆች በዚሁ የልማታዊነት ትግልና ጉዞ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማበርክት ከንቅናቄው ጎን ጸንተው እንዲቆሙ ደኢህዴን ጥሪውን እያቀረበ በክልላችን ድህነት ፈጥኖ እንዲሸነፍ ንቅናቄው ከመቼውም ጊዜ በላይ ብቁና ጠንካራ አመራር ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን ያረጋግጣል። መጪው ጊዜ የልማትና የሰላም ውጥኖች ስኬት የሚረጋገጥበት እንዲሆን ደኢህዴን ምኞቱን ይገልፃል።

ድልና ድምቀት ለድርብ በዓላችን!
ዘላለማዊ ክብር ለትግሉ ሰማዕታት!              
የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽ/ቤት
ግንቦት 2004 
ሀዋሳ


  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 394 guests