ከ681 ሺ በላይ ተማሪዎች የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚዎች ሆነዋል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 9/2004 (ዋኢማ)- በስድስት ክልሎች ከ681 ሺ በላይ ተማሪዎች በትምህርት ቤቶች በሚካሄደው የምገባ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ገለጹ።
ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን በአዲስ አበባ ለአራት ቀናት በሚቆየው «የትምህርት ቤቶች ምገባ ፕሮግራም» ላይ በሚያተኩረው ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ እንደተናገሩት፤ ፕሮግራሙ እየተካሄደ ያለው በተባበሩት መንግሥታት የምግብ ፕሮግራም ድጋፍ አማካኝነት ነው።
ፕሮግራሙ የምግብ እጥረት ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ የሚኖራቸውን ተሳትፎ በማሳደግ በአግባቡ ለማጠናቀቅ እያገዛቸው መሆኑን አመልክተዋል።
አቶ ደመቀ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ በትምህርት ቤቶች የሚካሄደው የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎች በትምህርታቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ በማድረግ መንግሥት የትምህርትን ጥራት ለማስጠበቅና ለማዳረስ ከጀመረው ጥረት ጋር በቀጥታ ግንኙነት አለው።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በስድስት ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 1ሺ 187 ትምህርት ቤቶች 681 ሺ 195 ተማሪዎች በምገባ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
በአርብቶ አደሮች አካባቢ ያለውን ከፍተኛ የጾታ ልዩነት ለማጥበብም «በልጃገረዶች ኢኒሼቲቭ ፕሮግራም» አማካኝነት ከ127 ሺ በላይ ሴቶች ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው።
ሚኒስትሩ ፕሮግራሙ በሚካሄድባቸው በደቡብ ክልል ሁለት ወረዳዎች በአካባቢው የሚመረቱ የምግብ ምርቶችን በአነስተኛ ማሳ ከተሰማሩ አርሶ አደሮች ላይ በመግዛት የምገባ ፕሮግራም በማካሄድ ባለፉት ወራት የሙከራ ሥራ ተጀምሯል።
በአካባቢ የሚመረቱ የምግብ ሰብሎችን ዋነኛ የምግብ ምንጭ በማድረግ የሚከናወኑ የተማሪዎች የምገባ ፕሮግራሞች በርካታ ጠቃሜታዎች እንዳሉት የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ የማህበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም በማሳደግ፣ ረሃብን በመቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥና ድህነትን መቀነስ እንዲሁም የሥራ ዕድል መፍጠርን ለአብነት ጠቅሰዋል።
ፕሮግራሙ በአካባቢው የሚመረቱ የምግብ ሰብሎችን በመግዛት ለተማሪዎች ምግብ ግዥ የሚወጣውን 80 በመቶ ገንዘብ ለማስቀረት አቅም እንደሚፈጥርም ሚኒስትሩ አስረድተዋል።
በአካባቢው የሚገኙ አነስተኛ አርሶ አደሮችም ከምርቱ ፍላጎት በመነሳት ከፍተኛ መጠን ያለው ምርት በማምረት የተሻለ ገቢ ለማግኘት ፍላጎት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያስችላል።
ፓርትነርሺፕ ፎር ቻይልድ ዴቬሎፕመንት የተባለው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሌስሊ ድራክ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች ውስጥ በየቀኑ በትምህርት ገበታ ላይ ከሚገኙ ሕፃናት መካከል 60 ሚሊዮኑ የምግብ እጥረት እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
የተራቡ ሕፃናት በትምህርት ገበታቸው ላይ ተገኝተው የሚሠጣቸውን ትምህርት በአግባቡ ለመከታተል እጅጉን ያዳግታቸዋል ሲሉም ተናግረዋል።
በተማሪዎች ምገባ ፕሮግራም ዙሪያ በሚመክረው «14ኛው የዓለምአቀፍ ዓመታዊ የሕፃናት ሥርዓተ ምግብ ጉባዔ» ታዋቂ ዓለም አቀፍ ባለሙያዎችን ያካተተ ሲሆን፣ ከሰሃራ በታች ከ23 አገሮች የተውጣጡ 200 የክፍለ-አህጉራዊ፣ብሄራዊና ዓለም አቀፍ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።
አዲስ ዘመን እንደዘገበው ጉባዔው ከሰሃራ በታች የትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራምን አስተማማኝ በማድረግ በኢኮኖሚ፣ በትምህርት፣ በግብርና ልማት ለማጠናከር በሚቻልበት ስልቶች ላይ ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


