የአፍሪካ ሀገራት ለሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እልባት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

  • PDF

አዲስ አበባ ግንቦት 8/2004/ ዋኢማ/ - የአፍሪካ ሀገራት ትኩረት ከሰጧቸው አንገብጋቢ አጀንዳዎች ጐን ለጐን ለሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እልባት የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ የወቅቱ የሕብረቱ ፕሬዝዳንት ጥሪ አቀረቡ።

በምርጫው ላይ የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ በሕብረቱ የተቋቋመው የመሪዎች ኮሚቴ በቤኒን ያደረገው ስብሰባ የደረሰበትን ሪፖርት በቀጣይ በማላዊ በሚካሔደው የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ አቅርቦ ጉዳዩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ በመስማማት ተጠናቋል።

በኮሚቴው ስብሰባ ምስራቅ አፍሪካን በመወከል የተካፈሉት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም ግንቦት 6 ሌሊት አዲስ አበባ ገብተዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ምርጫ እያስተናገደ የሚገኘውን ፉክክር አንዳንድ ወገኖች አሁን አሁን የልማት ስኬታቸው እየበረከተ በሚገኙ አፍሪካ ሐገራት የዴሞክራሲ ስርዓት የማበቡ ነፀብራቅ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ሕብረቱ ያሉበትን የሕግ ክፍተቶች ያጐላ ነው ይላሉ።

ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን የጉዳዩ በወቅቱ እልባት ማግኘት ሕብረቱ ባስቀመጣቸው ግቦች አፈጻጸም ላይ የላቀ ቦታ ይኖረዋል የሚል ሐሳብ የሚያነሱትም በሌላኛው ጫፍ የሚቀመጡ ናቸው።

በሊቀመንበሩ ምርጫ ላይ ለመምከር በሕብረቱ ጉባዔ የተቋቋመው የመሪዎች ኮሚቴ በመፍትሔ እርምጃዎች ላይ ውይይት ሲያደርግ የአሁኑ 2ኛው ነው።

ከወር በፊት በዚሁ በቤኒን ተገናኝቶ በሰፊው መክሮ የነበረ ሲሆን፤ እጩዎችን ያቀረቡት ደቡብ አፍሪካና ጋቦን በግል ተደራድረው ልዩነታቸውን እንዲያጠቡ ወስኖም ነበር።

ይሁንና ሁለቱ ወገኖች ወደ አንድ ሐሳብ መምጣት ባለመቻላቸው የአሁኑ ስብሰባ በቀጣይ በሚካሄዱ እርምጃዎች ላይ በዝግ መክሯል።

በውይይቱ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቤኒንና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ፕሬዝዳንት ቦኒ ያይ አፍሪካዊያን ቅድሚያ የሚሰጧቸው በርካታ ፈተናዎች ቢኖሩባቸውም የኮሚሽኑ ሊቀመንበር ምርጫ ቅድሚያ እልባት ሊያገኝ የሚገባው ጉዳይ ነው ብለዋል።

ውጤቱ በሕብረቱ የአጭርና የረጅም ግዜ ግቦች ስኬት ካለው ትርጉም አንጻር በበርካታ አፍሪካዊያን የሚጠበቅ መሆኑን በመግለፅ፤ ምስራቅ አፍሪካን የወከሉትን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ክፍለ አህጉራቱን የወከሉት መሪዎች በአሁኑ ውይይታቸው ማጠቃለያ የደረሰቡበትን ሪፖርት በመጪው ሐምሌ በማላዊ ለሚካሔደው 19ኛው የአፍሪካ ሕብረት ጉባዔ በማቅረብ በጠቅላላ ጉባዔው ውሳኔ እንዲሰጥበት ተስማምተዋል።

ከዚህ በተጨማሪም እጩዎችን ያቀረቡት ሁለቱ ሐገራት የሁለትዮሽ ውይይት ጐን ለጐን እንዲቀጥል ሪፖርቱ ለጉባዔው ከመቅረቡ በፊትም ኮሚቴው አንድ ጊዜ ተገናኝቶ እንዲመክርበት ከስምምነት መደረሱን የኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቭዥን ድርጅት ዘግቧል።









የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስፈጻሚውን በመቆጣጠር ረገድ የጀመረውን ጠንካራ እርምጃ እንዴት ያዩታል?




Results

ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የአባይን ወንዝ አቅጣጫ የማስቀልበስ ተግባር በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይከናወናል ብለው ገምተው ነበር




Results