ኤጀንሲው ደረጃውን የጠበቀ የአበባ ምርት ማሸጊያ ካርቶን ከዛሬ ጀምሮ ጥቅም ላይ እንደሚያውል አስታወቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 8/2004/ዋኢማ/ የኢትዮጵያ ሆርቲ ካልቸር ልማት ኤጀንሲ በሀገር ውስጥ የተመረተ ደረጃውን የጠበቀ የአበባ ምርት ማሸጊያ ካርቶን ከትናንት ጀምሮ ጥቅም ላይ እንደሚያውል አስታወቀ።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኃይለስላሴ ተክሌ ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የአበባ ምርቶች ደረጃውን በጠበቀ የማሸጊያ ካርቶን ታሽገው ከትናንት ጀምሮ እንደሚላኩ ይፋ አድርገዋል።
የአበባ ምርት ጥራትና ደረጃውን ጠብቆ ወደ ገበያ ለማቅረብ ከሚያስፈልጉት የድህረ ምርት ቴክኖሎጂ ውጤቶች አንዱ የማሸጊያ ካርቶን ነው።
የማሸጊያ ካርቶኑ የአበባ ምርትን ጥራት ለማስጠበቅና የምርቱን አገራዊ ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ጠቁመው፤ ቀደም ሲል ጥቅም ላይ የዋለው ማሸጊያ እስከ 30 በመቶ ድረስ በጥራቱ ላይ ተፅዕኖ ሲያሳድር እንደቆ የተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ የቀድሞ ማሸጊያ ደረጃውን ባለመጠበቁ የአበባ ምርቱን በሌላ አገር ምርት አስመስሎ የመሸጥ አዝማሚያም ተከስቷል።
በአሁኑ ወቅት የታዩ ክፍተቶችን በመገንዘብ ጥራቱንና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የማሸጊያ ካርቶን መዘጋጀቱንና በኢትዮጵያ ደረጃዎች መዳቢ ደረጃው መፅደቁን ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ ይህንንም ለማስፈፀም ከሁለት ዓመታት በላይ ጊዜ መውሰዱን ተናግረዋል።
ደረጃው ከፀደቀ በኋላም የማሸጊያ ካርቶኑን ማምረት የሚችሉ ፋብሪካዎች ብቃታቸው ተረጋግጦ ወደ ማምረቱ እንዲገቡ መደረጋቸውን ተናግረዋል።
እነዚህም አን ሊሚትድ ፓኬጂንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ፣ ቡራዩ ፓኬጂግና የህትመት ኢንዱስትሪ፤ ምናየ ፓኬጂንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ እና የኢትዮ ፕልፕና ወረቀት አክሲዮን ማህበር መሆናቸውን ጠቁመዋል።
አዲሱ የማሸጊያ ካርቶን ቀደም ሲል አበባ ላኪ ኩባንያዎች ከሚጠቀሙበት ደረጃውን ካልጠበቀ ማሸጊያ ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖረው በጥንቃቄ መሠራቱን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ ለዚህም ይረዳ ዘንድ አምራቾቹ ከውጭ የሚያስገቡት ጥሬ ዕቃ ከቀረጥ ነፃ እንዲሆን መደረጉን አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ በተስማሚነት ምዘና ድርጅት የሠርተፊኬሽንና የጥራት ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናታን መንገሻ በበኩላቸው፤ አራቱ ፋብሪካዎች በተሻለ የአመራረት ፣የጥራት ቁጥር ስልት መዘርጋትና የተሻለ ባለሙያ ያላቸው መሆኑ ለሥራው ተመራጭ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።
በቀጣይ ደግሞ ሌሎችም ፋብሪካዎች ደረጃቸውን በማሻሻል ማምረት እንደሚችሉ መናገራቸውን አዲስ ዘመን ጋዜጣን ጠቅሶ ኤፍቢሲ ዘግቧል።
| < Prev | Next > |
|---|


