ለማኑፋክቸሪንግ እድገት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ግንቦት 4/2004 (ዋኢማ)- አገሮች ለማኑፋክቸሪንግ እድገት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው በ22ኛው አለም አቀፍ የኢኮኖሚክ ፎረም ጉባዔ ላይ ተጠቆመ።
ዛሬ በሸራተን አዲስ ሁለተኛ ቀኑን በያዘው የውይይት መድረክ ላይ አገሮች የግብርና ምርታቸውን በማሳደግ የማኑፋክሪንግ ዘርፍን ለምጣኔ ሀብት እድገት በመጠቀም ህዝቦቻቸውን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባቸዋል።
ተወያዮቹ በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት ማኑፋክቸሪንግን በየሀገራቱ ለማስፋፋት የመንገድና የሀይል አቅርቦት ችግር እንዳለ ጠቁመው፤ እነዚህን ችግሮች በመቅረፍ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪን ማስፋፋት ተገቢ ነው ብለዋል።
ለዚህም የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባ የጠቆሙት የውይይት ተሳታፊዎች፤ ለልማት አማራጭ ሊሰጡ የሚችሉ ማኑፋክቸሪንም ኢንዱስትሪዎችን በስፋት ማስፋፋት ያስፈልጋል አፅንኦት ሰጥተው ተወያይተዋል።
በተለይም አፍሪካ ማኑፋክቸሪንግን ለማስፋፋት የተለያዩ ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ የሀይል አቅርቦትና የመሰረተ ልማቶችን በማስፋፋት ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባት አሳስበዋል።
በዚህም በሚቀጥሉት 20 አመታት የአፍሪካ የማኑፋክቸሪንግ ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ ተፈላጊ ሊሆን እንደሚችልም ተጠቁሟል።
ለዚህም አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋትና ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን የጠቆሙት ተወያዮቹ ጠንካራ የሆነ የንግድ አካባቢን መፍጠር፣ ግልፅ የሆነ የኢንዱስትሪ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሚሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት የናይጄሪያ የንግድና የኢንቨስትመንት ሚኒስትር ኦሉሴጉን አጋነጋ፣ የኬኒያው የኦርቢት ኬሚካል ኢንዱስትሪ ዋና ዳይሬክተር፣ የደቡብ አፍሪካ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሮብ ዳቪስ፣ የአሜሪካ ሴልድ ኤር ፕሬዚዳንድትና ዋና ስራ አስፈፃሚ ሚስተር ዊሊያም ቭ ሂኪይና ሌሎች ተሳታፊዎችም ተገኝተዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


