የሀብት ልዩነት የአህጉሪቱን እድገት እየተፈታተነ መሆኑ ተገለጸ

  • PDF

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2004 (ዋኢማ)- በአፍሪካ እየሰፋ የመጣው የሃብት ልዩነት የአህጉሪቱን የወደፊት እድገት እየተፈታተነው መምጣቱን  የአፍሪካ ፕሮግረስ ፓናል ገለጸ።

በ22ኛው የአለም ኢኮኖሚክ ፎረም በአፍሪካ ጉባዔ ላይ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተገለጸው በአህጉሪቱ እያደገ የመጣው ኢ-ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ችግር አህጉሪቱ የተያያዘችውን ጠንካራ የእድገት ጎዳና አደጋ ላይ እየጣለው መምጣቱ ተጠቁሟል።

ይህም የተገለፀው ዛሬ የአፍሪካ ፕሮግረስ ፓናል ዓመታዊ ሪፖርት ይፋ በተደረገበት ወቅት ሲሆን፤ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት በአህጉሪቱ ከአምስት በመቶ በላይ አመታዊ እድገት ይኖራል ተብሎ በሚጠበቅበት በአሁኑ ወቅት አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል ከእድገቱ ተጠቃሚ ባለመሆኑ አህጉሪቱ የተያያዘችው ጠንካራ እድገት አደጋ ያጠላበታል ተብሏል።

በመሆኑም ለዜጎች የስራ እድልን መፍጠር፣ ፍትሃዊነትን ማስፈን፣ እኩልነትን ማምጣትና በአህጉሪቱ ከፍተኛ ሀብት የሆነውን ወጣቱን ሃይል ተጠቃሚ በማድረግ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ ማስቀረት እንዳለባቸው በመግለጫው ተገልጿል።

ሪፖርቱ አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች እ.ኤ.አ በ2015 ለማሳካይ የታቀደውን የምዕተ አመቱን የልማት ግቦችን ሊያሳኩ እንደማይችሉ የጠቆመ ሲሆን፤ ጤና፣ ትምህርት፣ የህፃናትና የእናቶችን ሞት መቀነስና የተመጣጠነ ምግብ ችግርን በመቅረፍ የልማት እቅዶችን ከማሳካት አንፃር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ሪፖርቱ አስታውቋል።

እንደ ሪፖርቱ ገለፃ በሚቀጥሉት ሶስት አስርት ዓመታት በእጥፍ ይጨምራል ተብሎ በሚገመተው የአህጉሪቱ አጠቃላይ የህዝብ ብዛት ፍትሃዊና ሁሉንም በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ እድገት መፍጠር ግድ ይላል።

በመሆኑም የአፍሪካ ፖሊሲ አውጪዎች ስራ በመፍጠር፣ ፍትሃዊና ሁሉንም አፍሪካውያን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘላቂ እድገት ለማምጣት ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸውም ተጠቁሟል።

ይህ መሆን ካልቻለ ግን ከፍተኛ የሆነ የወጣቶች ስራ አጥነት፣ ማህበራዊ ህይወት መዛባትና ለርሃብ መጋለጥ ከመፈጠሩም በላይ በህብረተሰቡ ዘንድ የተረጋጋ ኑሮ የመምራት ሁኔታ ላይ ችግር ሊፈጥር እንደሚችል ሪፖርቱ ጠቁሟል።

በመሆኑም ሪፖርቱ መንግስታት የወጣቱን ስራ አጥነት፣  የትናንሽ ይዞታ ግብርና፣ የትምህርት ተደራሽነትና በመማር ማስተማር ላይና ሌሎች ጉዳዮች ላይ መፍትሄ ያስፈልጋቸዋል በማለት ለይቶ አስቀምጧቸዋል።

የፓናሉ ሊቀ-መንበርና የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሀፊ ሚስተር ኮፊ አናን በሪፖርቱ መግቢያ ላይ እንደገለፁት፤ በኑሮ እድሎች ላይ የሚታዩ ልዩነቶች በሚሊየን የሚቆጠሩ አፍሪካውያን ያላቸውን ሙሉ አቅም እንዳይጠቀሙ ከማድረጉም በላይ አጠቃላይ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ላይ እንቅፋት ይፈጥራል።

አፍሪካ ተመራጭ የኢንቨስትመንት መዳረሻና የዓለም የእድገት፣ የፈጠራ ግኝት ማዕከል መሆን በሚያስችላት ጎዳና ላይ እንደምትገኝ ጠቁመው፤ የዚህ ዓመት ሪፖርት አጠቃላይ መልዕክት ተስፋን የሰነቀ ከመሆኑም አንፃር የአህጉሪቱ መንግስታት በተለይም የተረሱና ችላ የተባሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

አፍሪካና መሪዎቿ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች በድል እንደሚወጡ እምነት አለኝ በማለት ለአፍሪካ መልካም ምኞታቸውን ተመኝተዋል።

በመግለጫው ወቅት ኮፊ አናንን ጨምሮ የቀድሞው የአለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ዳይሬክተር ሚካኤል ካማዴሱሰ፣ የአለምአቀፉ የኢንዱስትሪ ዘርፍ የትራንስፓረንሲ ኢንሼቲቭ ሊቀመንበርና መስራች ሚስተር ፔተር ኢግን፣ ታዋቂው ሙዚቀኛና የንግድ ሰው ቦብ ጌልዶፍ፣ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ ጨምሮ በርካታ እንግዶች ተገኝተዋል።


  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 153 guests