ኢትዮጵያ ለግብርና ልማት ከጠቅላላ በጀቷ 16 በመቶ መመደቧን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አስታወቁ
አዲስ አበባ ፤ግንቦት 3 2004 /ዋኢማ/ - ኢትዮጵያ ለግብርና ልማት ከጠቅላላ በጀቷ ከ16 በመቶ በላይ መድባ በመንቀሳቀስ ላይ እንደምትገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አስታወቁ።
በ22ኛዉ የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ የተሳተፉ አፍሪካ መሪዎች አፍሪካ የግብርናዉን ዘርፍ የበለጠ ለማሳደግ በአነስተኛ ማሳዎች ላይ ለሚካሄዱ የግብርና ሥራዎች ትኩረት መስጠት እንዳለባት ጠቁመዋል።
በሻራተን አዲስ ትናንት በተጀመረዉ የአለም ኢኮኖሚ ፎረም ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንዳስታወቁት የአፍሪካ ህብረት አባል አገራቱ የበጀታቸዉን አስር በመቶ ለግብርናዉ ዘርፍ ልማት እንዲመድቡ ካስቀመጠዉ መመርያ በተሻለ ኢትዮጵያ የበጀቷን 16 በመቶ ለዘርፉ መድባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በግብርና ልማት ላስመዘገበችዉ ስኬት መንግስት በአነስተኛ ማሳዎች ላይ ለሚካሄዱ እርሻዎች ትኩረት መስጠቱና የግል ባለሃብቶች በዘርፉ እንዲሰማሩ ያመቻቸዉ እድል ዋና ተጠቃሽ ናቸዉ።
የታንዛንያዉ ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዌቴ በበኩላቸዉ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ በአነስተኛ ማሳዎች ላይ የሚካሄዱ የግብርና ስራዎችን መደገፍና መንግስታት በግብርና ምርምር ላይ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ማሳደግ አለባቸዉ።
በዉይይቱ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪክዌቴን ጨምሮ የሳኡዲ አረቢያ የግብርና ሚኒስትር፣ የፔፕሲኮ አዉሮፓ ዋና ስራ አስፈጻሚ፣ የማላዊ የአነስተኛ እርሻ ገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር ዋና ስራ አስፈጻሚ እና የኔዘርላንዱ ሮቦ ባንክ የቦርድ አባል ተገኝተዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


