የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ለአህጉሪቱ ዕድገትና ለውጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተገለፀ
አዲስ አበባ ግንቦት 2/2004/ዋኢማ/ - የአፍሪካ የኢኮኖሚ ትስስር ለአህጉሪቱ ዕድገትና ለውጥ ትልቅ ፋይዳ እንዳለው በ22ኛው የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም የተሳተፉ ባለሀብቶችና የዓለም አቀፍ ኩባንያ ተወካዮች ገለፁ።
የአፍሪካን ትራንስፎርሜሽን ለማሳካት የቢዝነስ ተቋማት ሚና በሚል ርዕስ ከተለያዩ አህጉራት የተውጣጡ የንግድ ሰዎች፣ በአፍሪካ ኢንቨስት ያደረጉ የውጭ ሀገር ዜጎችና አፍሪካውያን ባለሃብቶች በሸራተን አዲስ ተወያይተዋል።
ውይይቱም በአፍሪካ በሚደረገው የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ሊያጋጥሙ በሚችሉ ችግሮችና አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ከአገር አገር ተንቀሳቅሰው ኢንቨስት በሚያደርጉበት ጊዜ ከአህገሪቱ ያገኙትን ተሞክሮ የተለዋወጡት ተሳታፊዎቹ በመድረኩ ላይ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ትስስር ለአህጉሪቱ እድገትና ለውጥ እንዲሁም ለኢንቨስትመንት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።
በአህጉሪቱ በአብዛኛው ወጣቶች ተምረው በቀላሉ ስራ እንደማያገኙ የገለፁት ተሳታፊዎቹ፤ ይህንኑ ችግር ለመፍታት ቀጣዮን ትውልድ ከስር ጀምሮ በንግድና በስራ ፈጠራ ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
በተጨማሪም በንግድና ሥራ ፈጠራ የሴቶችን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።
አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች አህጉር እንደመሆኗ ብዙ ሊሰራበት ይገባል ያሉት የውይይቱ ተሳታፊዎች ይህንኑ የተፈጥሮ ሀብት ወደ እሴት ለመለወጥ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ከአህጉሪቱ መንግስታት ጋር በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል።
በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ውጤት ለማምጣት በአህጉሪቱ የኤሌክትሪክ ሀይል አቅርቦት፣ የመረጃ መረብ ዝርጋታ፣ የትምህርትና የመሰረተ ልማት አቅርቦት መሟላት ወሳኝ እንደሆነም በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
ውይይቱን ከናይጄሪያ፣ ከኬንያ፣ ከደቡብ አፍሪካ፣ ከታንዛንያ፣ ከእንግሊዝና ከካናዳ የተዉጣጡ ባለሀብቶችና የትልልቅ ኩባንያ ሀላፊዎች መርተውታል።
| < Prev | Next > |
|---|


