ኮሚሽኑ በወረራ ተዘርፈው የነበሩ 435 የከተማ ቦታዎችን ማስመለሱን አስታወቀ
ሀዋሳ ሚያዚያ 29 2004 /ዋኢማ/ - በደቡብ ክልል በሙሰኞች አና በመሬት ወራሪዎች ተዘርፈው የነበሩ 435 ተጨማሪ የከተማ ቦታዎችን ማስመለሱን የክልሉ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንዳስታወቀው በሙሰኞችና በዘራፊዎች ተወስደው የነበሩት ቦታዎች ሰሞኑን የተመለሱት ኮሚሽኑ ከሕዝብ በደረሰው ጥቆማ በመነሳት ባደረገው ክትትል ነው፡፡
የከተማ ቦታዎቹ የተመለሱት በክልሉ በሃድያ ዞን ሆስዕና ከተማ መሆኑን በኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ደጋፊ የሥራ ሂደት ተወካይ ወይዘሮ ምንትዋብ አበበ ገልጸዋል፤፤
በአሁኑወቅት ቦታዎቹ ወደ መሬት ባንክ ተመላሽ ከመደረጋቸውም በላይ ይህንኑ የመንግሥትና የሕዝብ ሀብት ለግላቸው ያዋሉ የከተማው አስተዳደር አመራሮችና ተባባሪዎቻቸውን በሕግ ለመጠየቅ የሚያስችል የምርመራ ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽኑ በክልሉ በዲላ ፤ በወላይታ ሶዶ ፤ በአረካ ፤ በቦዲቲ በአርባ ምንጭ ከተሞች በወረራ የተዘረፉ የከተማ ቦታዎችን የመለየት ሥራ በመካሄድ ላይ እንደሚገኝና በቅርቡ ተመሳሳይ የማስመለስ እርምጃዎችን እንደሚወሰድ ተወካይዋ አመልክተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ መረጃዎችን በማሰባሰብ ባከናወነው የተጠናከረ የክትትልና የምርመራ ሥራ በሙሰኞቹ ተመዝብሮ የነበረ ከ 48 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ለማስመለስ መቻሉን ቀደምሲል ለዋልታ ገልጾ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ተመላሽ ከተደረገው ገንዘብ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆነው በሀዋሳ ከተማ አስተዳደር እና በሲዳማ ዞን የኦሞ ማይክሮ ፋይናንስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ሲያገለግሉ በነበሩ የሥራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች የተመዘበረ እንደነበር ተመልክቷል፡፡
እንደ ዋልታ ዘገባ ከሆነ በአሁኑወቅት የሃላፊዎቹና የባለሙያዎቹ ጉዳይ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ይገኛል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


