ሃይማኖት ሽፋን በመካሄድ ላይ ያለውንና ኢ-ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ለመጓዝ የመረጠውን ሃይል እንቅስቃሴ አስመልክቶ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር የተሰጠ መግለጫ

  • PDF

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሃይማኖታዊ ሽፋንን በመጠቀም በህዝቦች ትግልና ከፍተኛ መስዋዕት የተገነባውን የሃይማኖት እኩልነትና ማህበራዊ ሰላምን የሚያደፈርሱ አዝማሚያዎችና እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች በመከሰት ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ረገድ ተጠቃሽ ከሚሆኑት መካከል ላለፉት አስራ አንድ ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ አንዳንድ መስጊዶችና በዋናነትም በአወሊያ ትምህርት ቤት አካባቢ ህግና ስርዓት አክብረው ለመንቀሳቀስ ፍላጎትና ዝግጁነት በሌላቸው አንዳንድ ወገኖች በመካሄድ ላይ ያለው ፈፅሞ አግባብነት የሌለው እንቅስቃሴ አንዱ ነው፡፡ ይህ ከህጋዊነትና ህገመንግሥታዊ ስርዓት ይልቅ ኃይልና ህገወጥነትን በመስበክ ላይ የሚገኝ እንቅስቃሴ፣ ለፖለቲካ አላማው መጠጊያ አድርጎ የተጠቀመባቸው ሃይማኖታዊ ሽፋን ያላቸው ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ካገኙ በኋላም ሳይቀር በቀጥታ በመንግሥት ላይ ያነጣጠረ የውዥንብርና ሃሰተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ በማካሄድ እና በአወሊያም ሆነ በሌሎች መስጆዶች ሰፊው ሕዝበ ሙስሊም በሰላም ፀሎቱን አድርሶ ወደ ጉዳዩ ለመንቀሳቀስ የማይችልበትን ሁኔታ በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ ይህ ቡድን ይባስ ብሎም ህገወጥ አካሄዱን በይፋ ከቦታ ቦታ ለማስፋፋትና በከባድ መስዋዕትነት የተገነባውን የሃይማኖት እኩልነት፣ መቻቻልና ሰላም ለመናድ ዘመን አመጣሽ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም ለከፍተኛ ጥፋት እየተዘጋጀ ይገኛል፡፡ መንግሥት ለህዝበ ሙስሊሙና ለሚከተለው እምነት ካለው ጥልቅ አክብሮት በመነሳት የሚያሳየውን ትዕግስት እንደፍርሃት መመልከት የጀመረው ይህ ኃይል በአሁኑ ጊዜ ከውጭ ኃይሎች ጋር በተቀናጀ አኳኋን የሚያካሂደው ህገወጥ እንቅስቃሴ መረን የለቀቀበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

እንደሚታወቀው ሁሉ በአገራችን የሃይማኖት እኩልነት ህግመንግሥታዊ ዋስትና አግኝቶ ከተከበረ ሁለት አስርት ዓመታት ያህል ተቆጥሯል፡፡ በአገራችን የሚገኙ የተለያዩ ነባርና አዳዲስ ሃይማኖቶችን በእኩልነት ማስተናገድ ተስኖት የኖረው የአምባገነኖች ዘመን በመላ የአገራችን ህዝቦች ትግል ከተገረሰሰ በኋላ የሃይማኖት እኩልነት የተሟላ ህገመንግሥታዊ እውቅናና ዋስትና አግኝቶ ተከብሯል፡፡ በሀገራችን መንግሥትና ሃይማኖት እንዲነጣጠሉ በመደረጉ መንግሥታዊ ድጋፍ የሚደረግለት ወይም መንግሥታዊ ጫና የሚደርስበት አንድም ሃይማኖት የለም፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት አስተዳደር ጉዳይ እጁን አያስገባም፡፡ ትምህርትና ሃይማኖትም እንዲሁ እንዲነጣጠሉ ተደርገዋል፡፡ ዜጎች የመሰላቸውን እምነት በነፃነት የመከተል፣ ህግና ስርዓቱን ተከትለው ሃይማኖታዊ እምነታቸውን በፈለጉት አኳኋን የመግለፅ፣ የየራሳቸውን ሃይማኖት በግልና በወል እያመለኩ አገራቸውን በጋራ የመገንባት ሰፊ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በህገመንግሥታችን የተደነገጉ ሃይማኖታዊ የእኩልነት መብቶች ተግባራዊ በመደረጋቸው የትኛውም ሃይማኖት ከመንግሥት በኩል አድልዎና በደል ተፈጿመብኝ ሊል የማይችልበት፣ አዲስ የእኩልነትና የመቻቻል ስርዓት ተገንብቷል፡፡ ስለሆነም  በአገራችን የሚገኙ የተለያዩ የሃይማኖት እምነት ተከታዮች ከማንም ተፅዕኖ ነፃ በሆነ መንገድ እምነታችውን እየተከተሉና እየገለፀ ይገኛሉ፡፡ ይህ አውቆ ለተጨፈነና በሃይማኖት ሽፋንም የተሸሸገ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ለሚንቀሳቀስ ኃይል ካልሆነ በስተቀር ለመላ ኢትዮጵያውያን ግልፅ ሆኖ ያደረ ጉዳይ ነው፡፡

ሃቁ ይህ ሆኖ እያለ ከዚህ ቀደም በአንዋር መስጊድ ብጥብጥና ሁከት ቀስቅሰው ለዜጎች ህይወት መጥፋት ምክንያት በመሆናቸው በፍርድ ቤት የተበየነባቸውን ቅጣት ጨርሰው የወጡ አንዳንድ ግለሰቦችን ጨምሮ ሌሎች ተመሳሳይ አላማ ያነገቡ አንዳንድ ሰዎች ሃይማኖታዊ መልክ ያላቸው ጉዳዮችን መጠጊያ በማድረግ በሰፊ የጥፋት ቅስቀሳ ውስጥ ገብተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የራሳቸው የጥፋት አላማ ያላቸው ግለሰቦች መጀመሪያ በአወሊያ ትምህርት ቤት ሽፋን ላቀረቡት ጥያቄ ህገመንግሥቱን መሰረት ያደረገ ተገቢ ምላሽ ተሰጥቷቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ የእስልምና ጉዳዮች  ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሄድ ለቀረበ የበርካታ ሙስሊሞች ጥያቄም ጉዳዩ የሙስሊሙን ማህበረሰብ እንጂ መንግሥትን ስለማይመለከት ምርጫው በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ በምክር ቤቱ ማረጋገጫ የተሰጠበት ምላሽ አግኝቶ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ምንም እንኳ ሁለቱ የተለያዩ ጥያቄዎች የማያሻማ ምላሽ ያገኙ ቢሆንም በሃይማኖት ሽፋን ሁከት ለመፍጠር ቆርጠው የተነሱት እነዚህ ወገኖች ግን ለጥያቄዎቹ መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው የህዝበ ሙስሊም ተቋም የየራሳቸውን ምላሽ እንዳልሰጧቸው በማስመሰል ሰፊ አፍራሽ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ማካሄዳቸውን ቀጥለዋል፡፡

ከዚህም አልፎ በ97 ምርጫ አገሪቱን ለብጥብጥ ዳርገው ከፍ ያለ ጉዳት ካደረሱትና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተመደቡ ኃይሉች የጥፋት እንቅስቃሴ ጋር በግላጭ ተመጋጋቢ የሆነ ዘመቻም ማካሄድ ጀምረዋል፡፡ የኃላፊነት ስሜት በጎደለውና በአጉል ጀብደኝነት በታወረው ምግባራቸውም ማህበራዊ ሰላምን የሚያናጋ ግጭት ለመጫርና ለመቀስቀስ ሲንቀሳቀሱ ከርመዋል፡፡ መንግሥት መላ ቀልቡን ሌሎች ልዩ ልዩ ታላላቅ አገራዊ ተግባራትን ለመፈጿምና የህዝብን የኢኮኖሚና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ በሚያውልበት በዚህ የጿረ-ድህነት ትግል ወቅት፣ በአልባሌ ጉዳዮች ላለመጠመድ ያደረገውን ጥንቃቄና በማሳየት ላይ ያለውን ትዕግስት ከድክመት የቆጠሩት እኒህ ወገኖች ይባስ ብለው መንግሥት ጿረ-ህገመንግሥት ሆኗል፡፡ ስለዚህም በህገ መንግሥቱ የተጎናጿፍናቸውን መብቶች ሊነጥቀን ተነስቷል በሚል አይን ያወጣ ቅስቀሳ ግጭት ለመጫር እስከመንቀሳቀስ ደርሰዋል፡፡ ፓልቶክና ፌስቡክን የመሳሰሉ ዘመናዊ ሚዲያዎችን ለፕሮፓጋንዳቸው በመጠቀምና ሁሌም በሀገራችን ግርግርና ሁከት እንዲስፋፋ ከሚሹ በሀገር ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች ከሚተላለፉ የውጭ ሚዲያዎች ጋር በመቀናጀት በአገሪቱ መንግሥት ላይ የሚያካሂዱት የማጥላላት ዘመቻም መረን የለቀቀበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ የዚህ እኩይ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻቸው ሰለባ ከሆኑ ተከታዮቻቸው መካከል አንዳንዶቹ በግላጭ ..ጅሃድ.. ወይም ሃይማኖታዊ ጦርነት እስከማወጅና በጿጥታ አስከባሪ ኃይሎች ላይ ግልፅ ጥቃት እስከመሰንዘር መድረሳቸውን  በቅርቡ በምዕራብ አርሲ ዞን በገደባ አሳሳ ወረዳ በአሳሳ ከተማ ያስነሱት ሁከት በቂ አስረጅ ነው፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ላለፉት አስራ አንድ ሳምንታት ከቦታ ቦታ እየተጠራሩ በመስጊዶች የሚካሄደውን ሃይማኖታዊ ስርዓት በማወክ ላይ የተሰማሩት እነዚህ ወገኖች በአካባቢው ህግና ስርዓት ለማስከበር በተሰማሩ የፖሊስ ኃይሎች ላይ ተደጋጋሚ ድብደባና ትንኮሳ በመፈጿምም የተለያዩ ጉዳቶችን አድርሰዋል፡፡ ለአብነትም አርብ ሚያዝያ 12 ቀን በአንዋር መስጊድ አካባቢ ጿጥታ በማስከበር ተግባር ላይ ተሰማርተው ከነበሩ የፖሊስ አባላት መካከል ምክትል ሳጂን ብርሃኑ ብዙነህን በመደብደብ ጉዳት አድርሰውበታል፡፡ በአወሊያ ትምህርት ቤት አካባቢ በተደጋጋሚ መንገድ በመዝጋትና በፖሊስ ላይ ድንጋይ በመወርወር ግጭት ለመቀስቀስ ያልተሳኩ ጥረቶችንም አድርገዋል፡፡ በአንዋር መስጊድ ውስጥ የሚገኘውን ፅህፈት ቤት መስኮቶችም ሰባብረዋል፡፡ በነፋስ ስልክ አልፈትህ መስጊድ፣ በቦሌ ጃእፋር መስጊድና በፒያሳ በኒን መስጊድ የስግደት ስርዓቱን የሚመሩ የሃይማኖት አባቶችን ማይክሮፎን እየነጠቁ በመስጊዶች ውስጥ ሰላምና መረጋጋት እንዲጠፋ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ ጎተራ፣ እህል በረንዳ፣ በኒን ሰፈርና ሳሪስ በሚገኙ የመስጊድ ኢማሞችና የሃይማኖት አባቶች ላይም አደራጅተው በላኳቸው ጀሌዎቻቸው አማካይነት የድብደባ ጉዳት አድርሰዋል፡፡ እነዚህ ጀሌዎቻቸው የለቡ መስጊድንም ለማቃጠል ሙከራ አድርገዋል፡፡ በበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ላይም ህይወታችሁን እናጠፋለን በማለት የተቀናጁ የዛቻና የማስፈራራት ድርጊቶችን ፈፅመዋል፡፡ በቅርቡ ደግሞ ከአማራ፣ ከትግራይና ከኦሮሚያ አካባቢዎች የመለመሏቸውና ለህገወጥ ተልዕኮ ያሰማሯቸው 13 ያክል ተከታዮቻቸው በቄሌም ወለጋ ዞን በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ እነዚህ ህገወጥ ተግባራት በሃይማኖት ሽፋን አፍራሽ አቅጣጫን መከተልን የመረጠው ይህ ኃይል ከፈጿማቸው በርካታ ህገወጥ ተግባራት መሀል ለአብነት የተቀነጨቡ ጥቂት ማሳያዎች ናቸው፡፡

መንግሥት ይህን የመሰለውን ህገወጥና አስነዋሪ ድርጊት ከዛሬ ነገ ይታረማል በሚል ተስፋና ትዕግሥት ችግሩን ለማለዘብ በማሰብ የንቅናቄው መሪ ነን ከሚሉ ሰዎች ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን አድርጓል፡፡ በቅን ልቦና ባደረጋቸው በነዚህ ውይይቶች መግባባት ላይ ተደርሷል የሚል እምነት አሳድሮ መንቀሳቀስ ይቀጥል እንጂ ሃይማኖትን በሽፋንነት ለመጠቀም ቆርጠው የተነሱት እነዚህ ወገኖች ግን በስብሰባዎቹ ማግስት በመንግሥት ላይ ሰፊ የማጥላላት ዘመቻ መክፈታቸው የተለመደ ሆኗል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት በትዕግስትና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ከሁሉም በላይ ደግሞ በሙስሊሙ ማህበረሰብ አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት በመተማመን ጉዳዩን ለመፍታት ጥረት ከማድረግ አልተቆጠበም፡፡ ነገር ግን አጉል ጀብደኝነት በተጠናወተው አቅጣጫ መጓዝን የመረጡት እኒህ ወገኖች መንግሥት መቸም ቢሆን የማይሻገራቸው ቀይ መስመሮች እንዳሉ እያወቁ በሚያከናውኑዋቸው የጥፋት ተግባሮች ህገመንግሥታዊውን ስርዓት በመፈታተን ላይ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት ማንኛውም ሃይማኖታዊ ጥያቄ የሚስተናገድበት ህገመንግሥታዊ ስርዓት የተበጀ መሆኑን በጥብቅ በማስታወስ እኒህ ወገኖች በሃይማኖት ሽፋን ከሚያካሂዱት አፍራሽ ተግባርና ከተያያዙት የጥፋት መንገድ እንዲርቁና ህገመንግሥታዊ ስርዓቱን ተከትለው ብቻ እንዲንቀሳቀሱ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

ህዝበ ሙስሊሙም ይህን ተገንዝቦ በስሙ እየማሉና እየተገዘቱ ወደጥፋት አዘቅት በመንደርደር ላይ ያሉትን እኒህን ወገኖች ገደቦችን በመጣስ ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ እንዲቆጠቡ ግፊትና ጫና ያደርግባቸው ዘንድ መንግሥት ጥሪውን ያቀርባል፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖቶች አገር መሆኗ በህግ ታውቆ ሁሉም ሃይማኖቶች በእኩልነት እንዲከበሩ በተደረገበት ዘመን በሃይማኖት ስም የሚደረግ እንቅስቃሴ የህዝብን ሰላምና ጿጥታ እስከማወክ ሊፈቀድለት የማይገባ መሆኑን በመገንዘብ ይህን ለጥፋት ያኮበኮበ ኃይል መላ የአገራችን ህዝቦችና የተለያዩ እምነቶች ተከታዮች እንደተለመደው በተባበረ አቋማቸው ወደህጋዊ መስመር እንዲያስገቡትም ጥሪውን በድጋሚ ያቀርባል፡፡

ሚያዝያ 25 ቀን 2004 ዓ.ም

አዲስ አበባ

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 193 guests