በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጭፍጨፋና ግድያ የፈፀሙ ፀረ ሰላም ሃይሎች ለህግ እንዲቀርቡ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ
ጋምቤላ፤ሚያዚያ 26 2004 /ዋልታ/ - በጋምቤላ ክልል በቅርቡ በሰላማዊ ሰዎችና በልማት አጋሮች ላይ ጭፍጨፋና ግድያ የፈፀሙ ፀረ ሰላም ሃይሎች በአስቸኳይ ለህግ ቀርበው ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች በሠላማዊ ሰልፍ ጠየቁ ፡፡
የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ትናንት ባካሄዱት ሠላማዊ ሰልፍ በቅርቡ በክልሉ በንፁሃን ዜጎችና በውጭ አገር ባለሙያዎች ላይ የተፈፀመውን አረሜናዊ ጭፍጨፋና ግድያ አውግዘዋል፡፡ ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡና ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙም ሠላማዊ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡቦንግ በከተማው ስታድየም ለተሰበሰበው ከአስር ሺ በላይ ለሚሆን ህዝብ ባሰሙት ንግግር ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ የክልሉን ሕዝብ ተቻችሎ የመኖር ባህል ለማደፍረስና የክልሉን ልማት ለማደናቀፍ የሚያደርጉት ጥረት እንደመይሳካ ተናግረዋል።
ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ ካለፉት ጥቂት ወራት ጀምሮ ርካሽ ዓላማቸውን ለማስፈፀም በንፁሃን ዜጎች ላይ እየፈፀሙት ያለው አረሜናዊ ተግባርም በማንኛውም መመዘኛ ተቀባይነት እንደማይኖረው ገልፀዋል፡፡
የክልሉ ልማት፣ ሰላምና መረጋጋት የማይዋጥላቸው ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ፤ህዝቡ በድህነትና በድንቁርና እንዲኖር የሚፈልጉ ከመሆናቸውም በላይ ሕዝቡ እርስ በርስ እንዲተላለቅና ክልሉ ወደ ትርምስ እንዲገባ የሚፈልጉ መሆናቸውንም አቶ ኡሞድ ተናግረዋል።
ፀረ-ሰላም ሃይሎቹ በክልሉ በአቦቦ፣በጎግ፣በጆርና በጋምቤላ ወረዳዎች ሰለማዊ ዜጎችን በመግደልና ንብረትን በማወደም የሚያራምዱት ርካሽ የጠባብነት አጀንዳ ፈጽሞ አንደማይሳካም ተናግረዋል፡፡
ጠባቦቹ ፀረ-ሰላም ሃይሎች በክልሉ ዘርና ቀለምን ለይቶ የሚፈጽሙት የወንጀል ድርጊት በዝምታና በቸልታ የሚታይ አይደለም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ የጥፋት መረባቸውን ለመበጣጠስና በህብረተሰብቡ ውስጥ ያደፈጡ አረመኔዎችን ነቅሶ በማወጣት ለሕግ ለማቅረብ የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግስትናከክልሉ ሕዝብ ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን አቶ ኡሞድ ጠቁመዋል ፡፡
ልማትና ሰላም ወዳድ የሆነው የክልሉ ሕዝብም ከመንግስት ጎን በመቆም ፀረ-ሰላም ሃይሎቹን አጥብቆ እንዲታገል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ አቶ ቦል ኬት በበኩላቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት በከተማውና በክልሉ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖ የህዝቡ ተጠቃሚነት እየተረጋገጠ ባለበት በአሁኑ ወቅት ጸረ ሰላም ሃይሎቹ ዘር ለይተው እያከናወኑ ያሉት አረመነያዊ ተግባር ዘግናኝ ከመሆኑም በላይ የከተማውን የልማት እንቅስቃሴ የሚገታ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
መንግስት የአምስት ዓመቱን የዕድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ደፋ ቀና በሚልበት በአሁኑ ወቅት የጸረ ሰላም ሃይሎች የሽብር ተግባር የመያሳዝን መሆኑን በመጠቆም ይህንኑ እኩይ ተግባር ለመመከት ሁሉም በጋራ ሊረባረብ ይገባል ብለዋል፡፡
ጸረ ሰላም ሃይሎቹ ባለፉት ጊዜያት በጋምቤላ ትምህርትና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ተማሪዎችና በሳውዲስታር ኢንቨስትመንት ግሩፕ ሰራተኞች ላይ በፈፀሙት ጥቃት ከ24 በላይ ሰዎችን መግደላቸውና በርካታ ንፁሃን ዜጐችን ማቁሰላቸው ይታወቃል።
| < Prev | Next > |
|---|


