ባለሥልጣኑ በ45 ሚሊዮን ብር ወጪ ከዳያስፖራ አደባባይ እስከ ሰሜን ተርሚናል ያለውን መንገድ እየገነባ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ሚያዝያ 26 2004/ዋኢማ/ - የአዲስ አበባ መንገዶቸ ባለሥልጣን በ45 ሚሊዮን ብር ወጪ ከዳያስፖራ አደባባይ እስከ ሰሜን ተርሚናል ያለውን መንገድ ግንባታ እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ሁለት ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን መንገድ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንደሚጠናቀቅም ተገልጿል።

በአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች የሥራ ሂደት መሪ አቶ ሲሳይ ወርቅነህ ለዋልታ እንደገለጹት ከዳያስፖራ አደባባይ እስከ ሰሜን ተርሚናል ያለው የሁለት ነጥብ ሦስት ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ በ45 ሚሊዮን ብር ወጪ እየተከናወነ ነው።

የመንገዱን ግንባታ ባለሥልጣኑ በራሱ የሰው ኃይል እያካሄደ መሆኑን የተናገሩት የሥራ ሂደት መሪው ለመንገዱ ግንባታ የሚወለው ገንዘብ በመንግሥት የተመደበ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ በህዳር ወር 2004 ዓመተ ምህረት እንደተጀመረ የገለፁት አቶ ሲሳይ እስከአሁን በአዲሰ አበባ ከተማ ከተከናወኑ የመንገድ ፕሮጀክቶቸ ውስጥ የተሻለ አፈፃፀም የታየበት እንደሆነ ጠቁመዋል።መንገዱ ግንባታ በሁለት አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅም ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የመንገዱ ግንባታ የመጀመሪያ ምዕራፍ ሥራ የሆነው የአፈር ቆረጣና የሙሌት ሥራ እየተከናወነ ነው ያሉት አቶ ሲሳይ መንገዱ የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎለት በእስራኤል ኤምባሲ አካባቢ የድጋፍ ግንብ እየተገነባለት እንደሚገኝ  አብራርተዋል፡፡

መንገዱን በተሻለ ፍጥነት ለመጨረስ የወሰን ማስከበር፤የቴሌኮሚዩኒኬሽን፤የውሃ እና የመብራት መሥመሮችን ለማንሳት ባለሥልጣኑ ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በጋራ  እየሰራ መሆኑን  አስታውቀዋል፡፡

በአካባቢው በሥራ መግቢያና መውጪያ ሰዓት የሚከሰተውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ የመንገዱን ስፋት ከሰባት  ወደ ሰላሳ ሜትር ለማሳደግ መታቀዱን የተናገሩት አቶ ሲሳይ መንገዱ በቅርቡ ከተጠናቀቀው የመገናኛ ካራ መንገድ ጋር አንደሚገጥም  ገልጸዋል፡፡

የመንገዱ ግንባታ ሲጠናቀቅ ለኮተቤና ለአካባቢው ነዋረዎች  የተሻለ የሥራ ዕድል በመፍጠር  የራሱ  አሰተዋፅኦ እንደሚኖረው የተናገሩት ኋላፊው ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ ለሚደረገው ጉዞም እንደ አማራጭነት ያገለግላል ብለዋል።

ህብረተሰቡ በመንገዱ ግንባታ ወቅት የሚፈጠረውን የትራንስፖርት መስተጓጎል  ከግምት ውስጥ በማስገባት መንገዱ እስኪጠናቀቅ ሌሎች መንገዶችን በአማራጭነት እንዲጠቀምም ጠይቀዋል፡፡

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 195 guests